“አይሆንም! እኛ ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሉአት። ናዖሚም እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ! እባካችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለመሄድ የምትፈልጉት ለምንድነው? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች እንደገና መውለድ የምችል ይመስላችኋልን? ልጆቼ ሆይ! ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ሌላ ባል እንዳላገባ ዕድሜዬ አይፈቅድልኝም፤ ለመሆኑ ለማግባት ተስፋ ቢኖረኝና ዛሬውኑ አግብቼ ልጆች ብወልድስ፥ እነርሱ ለአካለ መጠን እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በዚህስ ምክንያት ሌሎች ባሎች ሳታገቡ ትቀራላችሁን? ልጆቼ ሆይ! ይህ የማይሆን ነው፤ እኔን እግዚአብሔር ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ” አለቻቸው። እነርሱም እንደገና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ ዖርፋ ዐማትዋን ስማ ተሰናበተች፤ ሩት ግን ከዐማትዋ ላለመለየት ወሰነች። ስለዚህ ናዖሚ “ሩት ሆይ! የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖችዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ከእርስዋ ጋር ተመለሺ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለቻት፦ “ተለይቼሽ እንድመለስ አታስገድጅኝ! አንቺ ወደምትሄጂበት ሁሉ እሄዳለሁ፤ አንቺ በምትኖሪበት እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ሩት ከእርስዋ ጋር ለመሄድ ቊርጥ ሐሳብ ማድረጓን በተረዳች ጊዜ፥ ናዖሚ ሌላ ነገር አልተናገረችም። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ወደ ቤተልሔም ተጓዙ፤ ቤተልሔም ሲደርሱም የከተማው ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፤ እዚያም ያሉ ሴቶች በመደነቅ “በእርግጥ ይህች ናዖሚ ናትን?” አሉ። እርስዋም እንዲህ አለች፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን መራራ ስላደረገው ‘ማራ’ በሉኝ እንጂ ‘ናዖሚ’ ብላችሁ አትጥሩኝ፤ ከዚህ አገር በሄድሁ ጊዜ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ እግዚአብሔር ግን ባዶ እጄን መልሶኛል፤ ታዲያ ሁሉን የሚችል አምላክ ሲፈርድብኝና ይህን ሁሉ ችግር ሲያደርስብኝ ‘ናዖሚ’ ብላችሁ ለምን ትጠሩኛላችሁ?” እንግዲህ ናዖሚ ከሞአባዊት ምራትዋ ከሩት ጋር ከሞአብ አገር የተመለሰችው በዚህ ሁኔታ ነበር፤ እነርሱ ቤተልሔም በደረሱ ጊዜ የገብስ መከር የሚሰበሰብበት ወቅት መጀመሩ ነበር።
መጽሐፈ ሩት 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሩት 1:10-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች