ወደ ሮም ሰዎች 5:6-15

ወደ ሮም ሰዎች 5:6-15 አማ05

ገና ደካሞች ሆነን ሳለ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ። በጻድቅ ምትክ ሆኖ የሚሞት ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም በደግ ሰው ምትክ ለመሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ያስረዳል። እንግዲህ የጸደቅነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሆነ ይበልጡንም ከእግዚአብሔር ቊጣ የምንድነው በእርሱ አማካይነት ነው። እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነን ሳለ በልጁ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፤ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቅን በኋላ በልጁ ሕይወት አማካይነት ይበልጡን እንድናለን። ይህም ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነትም በእግዚአብሔር እንመካለን። በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአት ምክንያትም ሞት መጣ፤ እንዲሁም ሰው ሁሉ ኃጢአትን ስለ ሠራ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕግ በሌለበት ኃጢአት ራሱ እንደ ኃጢአት አይቈጠርም ነበር። ሆኖም እንደ አዳም ሕግን በመተላለፍ ኃጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሳይቀር ሞት ከአዳም አንሥቶ እስከ ሙሴ ድረስ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን አገኘ። ይህ አዳም ወደፊት ለሚመጣው ክርስቶስ ምሳሌ ነበረ። ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታው እንደ ሰው ኃጢአት አይደለም፤ በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት ብዙዎች እንደ ሞቱ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት የተገኘው የጸጋ ስጦታ ለብዙዎች ተትረፍርፎ ተሰጥቶአል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}