እኔ በወንጌል ቃል አላፍርም፤ የወንጌል ቃል በመጀመሪያ አይሁድን፥ ቀጥሎም አሕዛብን፥ እንዲሁም የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኀይል ነው። ጻድቅ በእምነት ሕይወትን ያገኛል ተብሎ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ጽድቅም በሥራ ስለ ታየ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሰው የሚጸድቀው በእምነት ነው። ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል። የሚቀጣቸውም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚገባቸውን እግዚአብሔር ራሱ ገልጦላቸው ያውቁ ስለ ነበር ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። እነርሱ እግዚአብሔርን ዐውቀውት ሳለ ለእርሱ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብርና ምስጋና አልሰጡትም፤ በሐሳባቸውም ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውል ልቡናቸውም ጨለመ፤ “ጥበበኞች ነን” ሲሉ ሞኞች ሆኑ። የማያልፈውን እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ ኀላፊ በሆነው በሰው ምስል፥ በወፍ፥ አራት እግሮች ባሉአቸው እንስሶች፥ በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሶች መልክ ለተሠራው ምስል ክብርን ሰጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው በገዛ አካላቸው ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ርኲሰት ለሞላበት ለክፉ ምኞታቸው ተገዢዎች እንዲሆኑ ተዋቸው። ይህም የሆነው የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለ ለወጡ፥ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስላመለኩና ስለ አገለገሉ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን። ሰዎች ይህን በማድረጋቸው ምክንያት እግዚአብሔር ለማይገባ አስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸው እንኳ የተለመደውን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ባልተለመደ ግንኙነት ለወጡት። እንዲሁም ወንዶቹ የተለመደውን ግንኙነት ከሴቶች ጋር ማድረግ ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ስለዚህ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ነገር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በሥጋቸው ይቀበላሉ። ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ አስነዋሪ ነገር እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። ስለዚህ በበደል፥ በክፋት፥ በሥሥት፥ በተንኰል፥ በምቀኝነት፥ በነፍሰገዳይነት፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በክፉ ምኞት ሁሉ የተሞሉ፥ እንዲሁም ሐሜተኞች ናቸው፤ የሰውን ስም የሚያጠፉ፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ሰውን የሚያዋርዱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን ለማድረግ ዘዴ የሚፈልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ጨካኞች ናቸው። “እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል” የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ ይህን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፥ እንዲህ የሚያደርጉትንም ሰዎች ያበረታታሉ።
ወደ ሮም ሰዎች 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮም ሰዎች 1:16-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች