እግዚአብሔር ሆይ! በችግር ላይ ስለ ሆንኩ ምሕረትን አድርግልኝ፤ ዐይኖቼ፥ ነፍሴና ሥጋዬ በሐዘን ደክመዋል። ሕይወቴ በሐዘን ዕድሜዬም በመቃተት አለቀ፤ በችግሬ ምክንያት ኀይል አጣሁ፤ አጥንቶቼም ደከሙ። እኔ የጠላቶቼ መሳለቂያ፥ ለጐረቤቶቼ አስደንጋጭ፥ ለሚያውቁኝም አስፈሪ ነኝ፤ በመንገድ ሲያዩኝም ከእኔ ይሸሻሉ። እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤ ተሰብሮ እንደ ተጣለ የሸክላ ዕቃ ሆንኩ። የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁ፤ በሁሉም አቅጣጫ ፍርሀት አለ፤ በእኔ ላይ ያሤራሉ፤ ሊገድሉኝ በማቀድ ያድማሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ እኔ በአንተ እታመናለሁ። እኔ ሁልጊዜ በአንተ እጅ ነኝ፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ። ወደ አገልጋይህ በፈገግታ ተመልከት፤ በዘለዓለማዊ ፍቅርህም አድነኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ በምጣራበት ጊዜ አታሳፍረኝ፤ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ ጸጥ ብለውም ወደ ሲኦል ይውረዱ። በጻድቅ ላይ በትዕቢትና በንቀት በኩራትም ስለሚናገር የሐሰት አንደበታቸውን ጸጥ አሰኝ። በአንተ ለመከለል ወደ አንተ ለሚጠጉ በሰዎች ሁሉ ፊት የምትሰጠው ለሚፈሩህ ያዘጋጀኸው ደግነት ምንኛ ትልቅ ነው! ከሚያሤሩባቸው ሰዎች በመኖሪያህ ጥላ ሥር ትደብቃቸዋለህ፤ ከመርዘኛ አንደበትም በከለላህ ትጠብቃቸዋለህ። በተከበበች ከተማ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በሚያስደንቅ ሁኔታ ዘላቂ ፍቅሩን የገለጠልኝ እግዚአብሔር ይመስገን! ከድንጋጤዬ የተነሣ ከፊትህ ያራቅኸኝ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን ርዳታህን ፈልጌ ለምሕረት ወደ አንተ ስጣራ ጩኸቴን ሰማህ። እናንተ ለእርሱ የተቀደሳችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ ለትዕቢተኞች ግን ተገቢ ቅጣታቸውን ይሰጣል። እናንተ በእግዚአብሔር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ ጠንክሩ፤ በርቱም።
መጽሐፈ መዝሙር 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 31:9-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች