ጥበብ ቤትዋን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችንም ለቤትዋ አቆመች። ላዘጋጀችውም ግብዣ ፍሪዳ ዐረደች፤ የጣፈጠ የወይን ጠጅም ጠመቀች፤ ገበታም ዘርግታ ማእድ ሠራች። ገረዶችዋም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ቆመው፥ “ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ!” እያሉ እንዲጣሩ አደረገች፤ ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች። “ና ያዘጋጀሁትን ምግብ ብላ! የጠመቅኩትንም የወይን ጠጅ ጠጣ! ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች ተለይ! በሕይወትም ትኖራለህ፤ በማስተዋልም መንገድ ወደፊት ተራመድ።” ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ስድብን ታተርፋለህ፤ ክፉውን ሰው ብትገሥጸው ጒዳት ይደርስብሃል። ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ይጠላሃል፤ ጠቢብን ሰው ብታርመው ግን ይወድሃል። ጠቢብን አስተምረው፥ በይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ ደግን ሰው አስተምረው፤ ዕውቀትን ይጨምራል። እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። በእኔ አማካይነት ዕድሜህ ይረዝማል፤ ለሕይወትህም ዓመቶች ይጨመራሉ። ጥበብ ቢኖርህ ጥቅሙ ለራስህ ነው፤ ፌዘኛ ብትሆን የምትጐዳው ራስህን ነው። ዕውቀትን ማጣት፥ እንደ ለፍላፊ፥ ምንም ነገር እንደማታውቅ ደንቈሮና ኀፍረተቢስ ሴት መሆን ነው። እርስዋ በቤትዋ በር ላይ ወይም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ትቀመጣለች፤ ሥራቸውን በቅንነት እየሠሩ በመንገድ የሚያልፉትን ሁሉ እንዲህ እያለች ትጣራለች፦ “እናንተ ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ወደ እኔ ኑ!” ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች፦ “ሰርቀው የሚጠጡት ውሃ ይጣፍጣል፤ ተሸሽገው የሚበሉትም እንጀራ ያስደስታል።” እርሱም ወደ ቤትዋ የሚሄዱ ሁሉ እንደሚሞቱና እስከ አሁንም ወደ ቤትዋ የገቡ ወደ ሙታን ዓለም ተሽቈልቊለው እንደወረዱ አያውቅም።
መጽሐፈ ምሳሌ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ምሳሌ 9:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች