መጽሐፈ ምሳሌ 6:1-35

መጽሐፈ ምሳሌ 6:1-35 አማ05

ልጄ ሆይ! ዕዳውን ለመክፈል ለማይችል ሰው አንተ ልትከፍልለት ቃል ብትገባ፥ በተናገርከው ንግግር ብትጠመድ፥ በገባኸውም ቃል ብትያዝ፥ ልጄ ሆይ! በዚያ ሰው ሥልጣን ሥር ሆነሃል ማለት ነው፤ ስለዚህ ከእርሱ ቊጥጥር ነጻ ለመውጣት ብትፈልግ ፈጥነህ ወደ እርሱ ሂድ፤ ዋስትናውንም እንዲያወርድልህ ለምነው። ይህንን ሳታደርግ አትተኛ፤ በዐይንህም እንቅልፍ አይዙር። ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ ወፍ ከወጥመድ እንደሚያመልጡ አንተም ራስህን አድን። አንተ ሰነፍ ወደ ጒንዳን ሄደህ መንገድዋን ተመልክተህ ጥበብን ቅሰም። ጒንዳኖች መሪ፥ አለቃ፥ ወይም ገዢ የላቸውም፤ ነገር ግን በበጋ ወራት ምግባቸውን ያከማቻሉ፤ በመከር ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ይሰበስባሉ። ታዲያ፥ አንተ ሰነፍ! የምትተኛው እስከ መቼ ነው? ከእንቅልፍህስ የምትነቃው መቼ ነው? “ጥቂት እተኛለሁ፤ ጥቂት አንቀላፋለሁ፤ እጄንም አጣጥፌ ለጥቂት ጊዜ ዐርፋለሁ” ስትል፥ ገና ተኝተህ ሳለ ድኽነትና ማጣት የጦር መሣሪያ እንደ ታጠቀ ወንበዴ በድንገት ይደርሱብሃል። ባለጌና ክፉ ሰው በየቦታው እየዞረ ነገር እያጣመመ ያወራል። እርሱም፥ ለማታለል በዐይኑ ይጠቅሳል፤ በእግሩ ያመለክታል፤ በእጁ ይጠቊማል። በጠማማ አእምሮው ዘወትር ክፉ ነገርን ለማድረግ ያቅዳል፤ ሁልጊዜ ጠብን ይዘራል። ስለዚህም በድንገት ጥፋት ይደርስበታል፤ ሊድን በማይችልበት ሁኔታ በቅጽበት ይወድማል። እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም እርሱ የሚጸየፋቸው ሰባት ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፦ በንቀት የሚመለከት ዐይን፥ ሐሰትን የሚናገር ምላስ፥ ንጹሖች ሰዎችን የሚገድሉ እጆች፥ ክፉ ሐሳብ የሚያፈልቅ አእምሮ፥ ወደ ክፋት ለመሮጥ የሚቸኲሉ እግሮች፥ በውሸት ላይ ውሸት እየጨመረ የሚናገር ምስክር፥ በወዳጆች መካከል ጠብ የሚያነሣሣ ሰው። ልጄ ሆይ! የአባትህን ትእዛዞች ፈጽም፤ እናትህ ያስተማረችህንም ከቶ አትተው፤ የእነርሱን መመሪያ ዘወትር ተከተል፤ ቃላቸውንም ዘወትር ጠብቅ፤ እነርሱም በጒዞህ ይመሩሃል፤ ስትተኛም ይጠብቁሃል፤ ስትነቃም ያነጋግሩሃል። የእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ እንደ መብራት፥ ትምህርቱም እንደ ብርሃን ያበሩልሃል፤ ተግሣጹ እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምራል። ከመጥፎ ሴት እንድትርቅና ከሌላ ሰው ሚስት አሳሳች ቃል እንድትጠበቅ ይረዱሃል። ቊንጅናዋን አትመኝ፤ በዐይንዋ ጥቅሻ አትማረክ። አንድ ወንድ ሴትኛ ዐዳሪዋን በአንድ እንጀራ ዋጋ ሊያገኛት ይችላል፤ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ማመንዘር ግን የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል። በጉያው እሳት ይዞ ልብሱ የማይቃጠልበት ሰው አለን? እግሩስ ሳይቃጠል ፍም ረግጦ ለመሄድ የሚችል ሰው አለን? ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ግንኙነት የሚያደርግ እንደዚሁ ነው፤ የሌላውን ሰው ሚስት የሚነካ ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ምግብ ቢሰርቅ ለሰዎች አስገራሚ ነገር አይሆንም። ቢያዝም የቤቱን ሀብት ሁሉ የሚያሸጥ ቢሆን እንኳ ሰባት እጥፍ አድርጎ ይከፍላል። የምንዝር ተግባር የሚፈጽም ሰው ግን ማስተዋል የጐደለው ነው፤ ሕይወቱንም በከንቱ ያጠፋል። ውርደትና ድብደባ ይደርስበታል፤ ሁልጊዜም እንደ ተዋረደ ይኖራል። ቅናት የባልን ቊጣ ያነሣሣል፤ በሚበቀልበትም ጊዜ አይራራም። ምንም ዐይነት ካሳ መቀበል አይፈልግም፤ የስጦታም ብዛት ቊጣውን አያበርድለትም።