መጽሐፈ ምሳሌ 10:1-17

መጽሐፈ ምሳሌ 10:1-17 አማ05

እነዚህ የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፤ ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል። አግባብ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ ቀጥተኛነት ግን ከሞት ያድናል። እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን እንዲራቡ አያደርግም፤ ክፉዎች ግን የተመኙትን እንዳያገኙ ያደርጋል። ስንፍና ያደኸያል፤ ተግቶ መሥራት ግን ያበለጽጋል፤ ብልኅ ሰው መከሩን በወቅቱ ይሰበስባል፤ በመከር ወራት የሚተኛ ግን ውርደት ይደርስበታል። ደግ ሰው በረከትን ያገኛል፤ ክፉ ሰው ግን ዐመፀኛነቱን በመልካም አነጋገር ይሸፍናል። የጻድቅ ሰው መታሰቢያ ለበረከት ይሆናል የክፉዎች ስም ግን ይጠፋል። በእውነት ጥበበኛ የሆነ ሰው ትእዝዞችን ይቀበላል፤ የሚለፈልፉ ሞኞች ግን ወደ ጥፋት ያመራሉ። በሁሉም ነገር ታማኝ ሰው ያለ ስጋት ይኖራል። የጠማማ ሰው እርምጃ ግን ይጋለጣል። በሰው ላይ መጠቃቀስ ችግርን ያመጣል፤ በግልጥ የሚነቅፍ ግን ሰላም እንዲገኝ ያደርጋል። የደግ ሰው ንግግር የሕይወት ምንጭ ነው፤ የክፉ ሰው ንግግር ግን የዐመፅ መሸፈኛ ነው። ጥላቻ ሁከትን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ አይታ በይቅርታ ታልፋለች። በአእምሮ የበሰሉ ሰዎች በማስተዋል ይናገራሉ። ሞኞች ግን ቅጣት መቀበል የሚገባቸው ናቸው። ጠቢባን በሚቻላቸው ዘዴ ሁሉ ዕውቀትን ያከማቻሉ፤ ሞኞች በሚናገሩበት ጊዜ ግን ጥፋት መምጣቱ አይቀርም። ባለጸጋን ሀብቱ እንደ ምሽግ ሆኖ ይጠብቀዋል፤ ድኻውን ግን ድኽነቱ ያጠፋዋል። የደግ ሰው መልካም ሥራ ሕይወትን ያስገኝለታል፤ የክፉ ሰው ኃጢአት ግን ቅጣትን ያስከትልበታል። ተግሣጽን የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ሕይወት መንገድ ያመራሉ፤ ከስሕተታቸው የማይማሩ ሰዎች ግን አደጋ ላይ ይወድቃሉ።