ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3:4-14

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3:4-14 አማ05

ትምክሕት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ በብዙ ነገር ልመካ እችላለሁ፤ በውጭ በሚታየው ሥርዓት የሚመካ ሰው ቢኖር እኔ ከእርሱ ይበልጥ የምመካበት ብዙ ምክንያት አለኝ። እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዤአለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ነገድ የሆንኩ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም የተነሣ ጥርት ያልኩ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁድን ሕግ ስለ መጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበር። ስለ ኦሪት ሕግ በመቅናትም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን አማኞች አሳድ ነበር። ሕግን በመጠበቅ ስለ መጽደቅም ቢሆን ያለ ነቀፋ እኖር ነበርኩ። እንግዲህ ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው ከንቱ ነገሮች አድርጌ እቈጥራቸዋለሁ። ከዚህም በቀር ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ስለማምን ሁሉን ነገር እንደ ኪሣራ እቈጥረዋለሁ፤ ስለ እርሱም ሁሉን ነገር አጥቻለሁ። ክርስቶስንም ለማግኘት ስል ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቈጥራለሁ። ይህንንም የማደርግበት ምክንያት በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴን ጽድቅ ትቼ በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ በማመን ለማግኘትና ከእርሱም ጋር ለመሆን ነው። ሌላው ምክንያት ክርስቶስንና የክርስቶስን የትንሣኤ ኀይል ለማወቅ፥ የመከራው ተካፋይ ለመሆንና በሞቱም እርሱን ለመምሰል ነው። እንዲሁም ከሞትኩ በኋላ ተነሥቼ ለዘለዓለም በሕይወት ለመኖር ተስፋ በማድረግ ነው። ይህን ሁሉ ገና አላገኘሁም፤ ወይም በዚህ ሁሉ ፍጹም ሆኜአለሁ ለማለት አልችልም፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔን የእርሱ አድርጎ ያዘጋጀልኝን ሽልማት ለማግኘት ወደፊት በመሮጥ እተጋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ! ገና ወደዚያ እንደ ደረስኩ አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ይኸውም በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}