እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገር፦ ወንድ ወይም ሴት ማንኛውም ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር በመለየት ናዝራዊ ለመሆን ስእለት ቢያደርግ፥ የወይን ጠጅም ሆነ ማናቸውንም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የተሠራ ሆምጣጤ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ፤ በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ሐረግ የሚገኘውን ሁሉ የወይኑን ፍሬ ግልፋፊ ወይም ዘር አይብላ። “ስእለት ተስሎ በናዝራዊነት እስካለ ድረስ ራሱን ምላጭ አይንካው፤ የናዝራዊነት ጊዜው እስኪፈጸም ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ (የተቀደሰ) ይሆናል፤ የራሱንም ጠጒር ያሳድጋል። በናዝራዊነት በአለበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሞተ ሰው በድን አይቅረብ፤ ለአምላኩ ያቀረበው የናዝራዊነት ስእለት በራሱ ላይ ስለ ሆነ አባቱ ወይም እናቱ፥ ወንድሙ ወይም እኅቱ ቢሞቱ አስከሬናቸውን በመንካት ራሱን አያርክስ። ናዝራዊ እስከ ሆነ ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ (የተቀደሰ) ነው። “በድንገት አንድ ሰው በአጠገቡ ቢሞት፥ የተቀደሰውን ራሱንም ቢያረክስ፥ በሰባተኛው ቀን ራሱን ይላጭ። በስምንተኛው ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት ርግቦች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደሚገኘው ካህን ያምጣ። ካህኑም አንዱን ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት፥ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ናዝራዊው ሬሳ በመንካቱ ስለ ረከሰ ያስተሰርይለታል፤ በዚያኑ ቀን ናዝራዊው ጠጒሩን እንደገና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ያደርገዋል። በናዝራዊነትም ለማገልገል ራሱን እንደገና ለእግዚአብሔር የተለየ ያደርጋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰው ጠጒሩ ከመርከሱ የተነሣ ከዚያ በፊት በናዝራዊነት የነበረበት ክፍለ ጊዜ አይቈጠርለትም፤ ስለ በደልም ለሚከፈለው ዋጋ አንድ ዓመት የሞላው የበግ ጠቦት ያምጣ። “አንድ ናዝራዊ የናዝራዊነት ስእለቱን ሲጨርስ የሚፈጽመው ሕግ ይህ ነው፦ ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ በር ሄዶ፥ እዚያ ቊርባኑን ለእግዚአብሔር ያቀርባል፤ ይኸውም ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላው የበግ ጠቦት፥ ስለ ኃጢአት ስርየት ለሚቀርበውም መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላት አንዲት የበግ ቄብ እንዲሁም የአንድነት መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ያቀርባል ማለት ነው። ደግሞም እርሾ ሳይነካው የተጋገረ አንድ መሶብ እንጀራ፥ በወይራ ዘይት ከተለወሰ ዱቄት የተጋገረ ውፍረት ያለው ኅብስት፥ በወይራ ዘይት የተቀቡ ስስ ቂጣዎች ጭምር ከሚቀርበው ከእህል ቊርባንና ከመጠጥ መባ ጋር አብሮ ይቅረብ። “ካህኑም ይህን ሁሉ የኃጢአት ስርየትና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባቸዋል። አውራውን በግ የአንድነት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀርበዋል፤ እርሱንም በመሶብ ካለው እንጀራ ጋር ያቀርበዋል፤ ቀጥሎም የእህሉን ቊርባንና የመጠጡን መባ ያቀርባል። በመገናኛው ድንኳን በር መግቢያ ላይ ናዝራዊው ጠጒሩን ላጭቶ የአንድነት መሥዋዕት በሚቃጠልበት እሳት ላይ ያኖረዋል። “ናዝራዊው የተቀደሰውን ጠጒሩን ከተላጨ በኋላ ካህኑ የተቀቀለውን አውራ በግ ወርች፥ በመሶብ ውስጥ ካለው አንድ ኅብስትና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊ በሆነው ሰው እጆች ላይ ያኖረዋል፤ ከዚህም በኋላ ካህኑ ይህን ሁሉ ወስዶ ለእግዚአብሔር የሚወዘወዝ ልዩ መባ አድርጎ ያቀርበዋል፤ ይህም ሁሉ የካህኑ ድርሻ ሆኖ ከሚነሣው ከአውራው በግ ፍርንባና ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል፤ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት የሚፈቀድለትም ከዚያን በኋላ ነው። “እንግዲህ እነዚህ ስለ ናዝራውያን የተሰጡ የሕግ መመሪያዎች ናቸው፤ ነገር ግን አንድ ናዝራዊ በስእለቱ መሠረት ሊያቀርብ ከሚገባው በላይ ለመስጠት ቃል ቢገባ በገባው ቃል መሠረት ስእለቱን መፈጸም አለበት።”
ኦሪት ዘኊልቊ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኊልቊ 6:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች