የማርቆስ ወንጌል 2:3-12

የማርቆስ ወንጌል 2:3-12 አማ05

በዚያን ጊዜ አራት ሰዎች አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው ወደ እርሱ መጡ። ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ቢያቅታቸው የቤቱን ጣራ ኢየሱስ ባለበት በኩል ከፍተው ሽባውን ከነአልጋው አወረዱት። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው። በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ የሕግ መምህራን በልባቸው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ለምን እንዲህ ያለ ስድብ በእግዚአብሔር ላይ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል ማን ነው?” ወዲያውኑ ኢየሱስ ይህን የልባቸውን ሐሳብ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን በልባችሁ ይህን ታስባላችሁ? ሽባውን፥ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል፤’ ከማለትና፥ ‘ተነሥተህ አልጋህን ተሸከምና ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሥልጣን ያለው መሆኑን እንድታውቁ” ብሎ ሽባውን፥ “ተነሥ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው። ሽባውም ወዲያውኑ ተነሣና አልጋውን ተሸክሞ በሰዎቹ ሁሉ ፊት ወጣ። ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይተን አናውቅም እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች