የማቴዎስ ወንጌል 27:45-54
የማቴዎስ ወንጌል 27:45-54 አማ05
ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ።

