የማቴዎስ ወንጌል 27:32-52
የማቴዎስ ወንጌል 27:32-52 አማ05
ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚህ በኋላ ትርጒሙ “የራስ ቅል” ወደ ሆነው ወደ ጎልጎታ ደረሱ። በዚያም ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ለኢየሱስ አቀረቡለት፤ እርሱ ግን ቀመስ አድርጎ ሊጠጣው አልፈለገም። ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ወንጀል የሚያመለክት፥ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው?” የሚል ጽሑፍ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ። በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች በንቀት ራሳቸውን እየነቀነቁ፥ “አንተ ቤተ መቅደስን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከመስቀል ውረድ!” በማለት ያላግጡበት ነበር። በዚሁም ዓይነት የካህናት አለቆች ከሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንመንበት! እርሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ።

