የማቴዎስ ወንጌል 15:21-31

የማቴዎስ ወንጌል 15:21-31 አማ05

ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች ሄደ፤ ከዚያም አንዲት ከነዓናዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ ትሠቃያለችና እባክህ ራራልኝ!” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ፤ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት!” ሲሉ ለመኑት። እርሱም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት እንደ በጎች ለጠፉት ብቻ ነው” ሲል መለሰ። ሴትዮዋ ግን ቀርባ በእግሩ ሥር ተንበረከከችና “ጌታ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ኢየሱስም “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል የተገባ አይደለም” አለ። እርስዋም “ጌታ ሆይ! እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ውሾችም ከጌቶቻቸው ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት እምነትሽ! ትልቅ ነው፤ ስለዚህ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ!” አላት። የሴትዮዋም ልጅ በዚያኑ ሰዓት ዳነች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራ ላይም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሰዎች አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ድዳዎችንና ሌሎችንም በሽተኞች ይዘው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ በእግሩም ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሳዎች በደኅና ሲራመዱ፥ ዕውሮች ሲያዩ በተመለከቱ ጊዜ ተደንቀው የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች