የማቴዎስ ወንጌል 12:22-37
የማቴዎስ ወንጌል 12:22-37 አማ05
ከዚህ በኋላ ሰዎች አንድ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ሰውየውም መናገርና ማየት ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው፥ “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “እርሱ ‘ብዔልዜቡል’ በተባለው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይወድቃል። እንዲሁም አንድ ከተማ ወይም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ ታዲያ፥ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊኖር ይችላል! ደግሞ እኔ አጋንንትን የማስወጣቸው በብዔልዜቡል ከሆነ፥ ልጆቻችሁስ በምን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ ልጆቻችሁ በእናንተ ላይ ይፈርዱባችኋል። እኔ አጋንንትን የማስወጣ በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ ግን እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት በእናንተ ላይ መጥታለች ማለት ነው። ደግሞስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን መዝረፍ እንዴት ይችላል? ኀይለኛውን ካሰረው በኋላ ግን በእርግጥ ንብረቱን ሊዘርፍ ይችላል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። ስለዚህ ሰው የሚያደርገው ማናቸውም ኃጢአት ወይም የስድብ ቃል ሁሉ ይቅር ይባልለታል እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሰው ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በደሉ ይቅር ይባልለታል። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በደሉ ይቅር አይባልለትም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ ፍሬውም መልካም ይሆናል፤ ዛፉ መጥፎ ከሆነ ግን ፍሬውም መጥፎ ይሆናል። እናንተ የእባብ ልጆች! ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? ሰው በአፉ የሚናገረው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “መልካም ሰው ከመልካም መዝገቡ፥ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገቡ ክፉ ነገርን ያወጣል። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች በግዴለሽነት በሚናገሩት በያንዳንዱ ቃል በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ከቃልህ የተነሣ ይፈረድልሃል፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃል።”


