የሉቃስ ወንጌል 4:1-22

የሉቃስ ወንጌል 4:1-22 አማ05

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተመለሰ፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ በረሓ ሄደ። እዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀኖች ምንም ስላልበላ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው። ኢየሱስም፦ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። “ይህን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ የተሰጠኝ ስለ ሆነ ለፈለግሁት መስጠት እችላለሁ፤ ስለዚህ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ለጌታ ለአምላክህ ብቻ ስገድ! እርሱንም ብቻ አምልክ! ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ በቤተ መቅደሱም ጣራ ጫፍ ላይ እንዲቆም አድርጎ፥ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ ከዚህ ወደታች ዘለህ ውረድ፤ ‘አንተን እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዛል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል፥ በእጃቸው ደግፈው ይይዙሃል፥’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው፥’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። ዲያብሎስ ኢየሱስን መፈተኑን ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ትቶት ሄደ። ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተሰማ። በምኲራቦቻቸውም ያስተምር ነበር፤ ሁሉም በትምህርቱ አመሰገኑት። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ አደገበት አገር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኲራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሰሩት መፈታትን፥ ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤ እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።” ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤ እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው። ስለ እርሱ ሁሉም መልካም ይናገሩ ነበር፤ በሚናገረውም ጸጋን የተመላ ቃል ተደንቀው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉ።