የሉቃስ ወንጌል 20:9-18

የሉቃስ ወንጌል 20:9-18 አማ05

ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎች አከራየውና ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ ሳይመለስም ብዙ ጊዜ ቈየ። ወይኑ ባፈራ ጊዜ የወይኑ ተክል ባለቤት ከፍሬው ድርሻውን እንዲቀበልለት አንድ አገልጋይ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው፥ ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት፤ እንደገናም ሦስተኛ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደብድበው አቈሰሉትና አውጥተው ጣሉት። ከዚህም በኋላ የወይኑ ተክል ባለቤት፦ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልከዋለሁ፤ እርሱን ምናልባት ያከብሩት ይሆናል!’ አለ። ነገር ግን ገበሬዎቹ ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ ‘ይህ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል!’ ስለዚህ ልጁን ከወይኑ ተክል ቦታ ወደ ውጪ አውጥተው ገደሉት። ታዲያ፥ እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? የወይኑ ተክል ባለቤት ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጣል።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ታዲያ፥ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ምንን ያመለክታል? በዚያ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”