የሉቃስ ወንጌል 15:17-32

የሉቃስ ወንጌል 15:17-32 አማ05

በዚህ ጊዜ ልጁ ስሕተቱን ተገንዝቦ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘በአባቴ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ አገልጋዮች እንጀራ እስኪጠግቡ በልተው የሚተርፋቸው ስንት ናቸው! እኔ ግን እዚህ በረሀብ መሞቴ ነው፤ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ልጅ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከቅጥረኞች አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ልበለው።’ ስለዚህ ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “አባቱም ገና በሩቅ ሳለ ልጁን አየው፤ ራርቶለትም ወደ እርሱ ሮጠ፤ ዕቅፍ አድርጎም ሳመው። ልጁም ‘አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም’ አለ። አባቱ ግን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ ‘ቶሎ ብላችሁ ከሁሉ የበለጠውን ልብስ አምጡና አልብሱት! በጣቱ ቀለበት፥ በእግሩም ጫማ አድርጉለት! የሰባውን ወይፈን አምጡና ዕረዱ! እንብላ! እንደሰት! ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፥ እነሆ፥ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኘ’፤ መደሰትም ጀመሩ። “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ ለሥራ ወደ እርሻ ወጥቶ ነበር፤ ተመልሶ ሲመጣ ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ‘ምንድን ነው ነገሩ?’ ብሎ ጠየቀው። አገልጋዩም ‘ወንድምህ ተመልሶ ስለ መጣ ነው፤ አባትህ በደኅና ስላገኘው የሰባውን ወይፈን ዐርዶለታል’ አለው። “ታላቅ ወንድሙም በጣም ተቈጥቶ፥ ‘ወደ ቤት አልገባም’ አለ። ስለዚህ አባቱ ወደ ደጅ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው፤ ልጁ ግን ለአባቱ እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘እነሆ! ይህን ያኽል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ ታዲያ እኔ ከጓደኞቼ ጋር የምደሰትበት አንድ ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም! ይህ ልጅህ ግን ሀብትህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በተመለሰ ጊዜ የሰባውን ወይፈን ዐረድክለት።’ አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው። ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ አሁን ተገኘ፤ ስለዚህ በጣም ልንደሰት ይገባናል።’ ”