እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ማንም ሰው በሰውነቱ ላይ እባጭ ወይም ሽፍታ ወይም ቋቊቻ ቢታይና በገላው ላይ የሥጋ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም ቊስሉን ይመርምር፤ በዚያም ቊስል ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ፥ ቊስሉም በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝ፥ እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ካህኑም ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ቊስሉ ነጭ ሆኖ በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጐድ ብሎ ባይገኝና ጠጒሩም ወደ ነጭነት ባይለወጥ፥ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ ካህኑ በሰባተኛው ቀን እንደገና ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ ምንም ለውጥ ሳያሳይ እንደ ነበረ ሳይስፋፋ ቢያገኘው፥ አሁንም ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። ካህኑም እንደገና በሰባተኛው ቀን ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ በመስፋፋት ፈንታ ከስሞ ከተገኘ፥ ቊስሉ እከክ ብቻ መሆኑን ገልጦ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ያም ሰው ስለ መንጻቱ ልብሱን ይጠብ፤ ነገር ግን ካህኑ መርምሮ ንጹሕ መሆኑን ካስታወቀለት በኋላ፥ ቊስሉ ተስፋፍቶ ቢገኝ ያ ሰው እንደገና በካህኑ ፊት ይቅረብ፤ ካህኑም እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉም ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ የረከሰ የሥጋ ደዌ በሽተኛ መሆኑን ያስታውቅ። “ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽታ ቢይዘው ወደ ካህኑ ያምጡት፤ ካህኑም ይመርምረው፤ በቈዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጒሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በቈዳው ላይ የቈየ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ካህኑ ሕመምተኛው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የረከሰ መሆኑ በግልጥ ስለ ታወቀ እንደዚህ ያለው ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት መቈየት አያስፈልገውም። እንደ ካህኑ አስተያየት የሥጋ ደዌው በሽታ ሰውየውን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጒሩ የሸፈነው ከሆነ፥ ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ መላ ሰውነቱን ሸፍኖት ቢያገኘው፥ ቆዳው በሙሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ የነጻ ስለሚሆን ካህኑ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅ፤ ነገር ግን በሥጋው ላይ የሚያዥ ቊስል ቢታይበት የረከሰ ይሆናል። ካህኑም እንደገና መርምሮት የሚያዥ ቊስል ቢያገኝ፥ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የሚያዥ፥ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ ነው። ቊስሉ ቢፈወስና እንደገና ወደ ነጭነት ቢለወጥ ግን እንደገና ወደ ካህኑ ይሄዳል፤ ካህኑም እንደገና መርምሮት ቊስሉ ወደነጭነት ተለውጦ ከተገኘ ያ ሰው የነጻ ይሆናል፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያሳውቅለታል። “አንድ ሰው የዳነ እባጭ ቢኖርበትና፥ ዘግየት ብሎም ቊስሉ ባለበት ቦታ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ዐይነት ቊስል ቢወጣበት ወደ ካህኑ ይሂድ፤ ካህኑም መርምሮት ቊስሉ ያለበት ቦታ ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝና በቈዳው ላይ ያለውም ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ እርሱም በእባጭ የተጀመረ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ካህኑ መርምሮት በቈዳው ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ባይለወጥና ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይበልጥ ጐድጒዶ ባይገኝ፥ የቀለሙ ልዩነት ስለ ተቀነሰ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ ቊስሉ ያለበትም ቦታ እየሰፋ መሄዱ ከታወቀ፥ ያ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ቋቁቻው ምንም ለውጥ ሳያደርግና ሳይስፋፋ ቢገኝ የእባጭ ጠባሳ መሆኑ ታውቆ መንጻቱን ካህኑ ያስታውቅለት። “የእሳት ቃጠሎ የደረሰበት ሰው ቢኖርና የተቃጠለ ሥጋው ቢነጣ ወይም ቀላ ያለ ነጭ ሆኖ ቢገኝ፥ ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ ባለበት ስፍራ የበቀለው ጠጒር ነጭ ቢሆንና ያም ስፍራ በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ከተገኘ፥ ከእሳት ቃጠሎ የመጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ካህኑ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ። ይህም የሥጋ ደዌ ነው። ነገር ግን በእርሱ ላይ የበቀለው ጠጒር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘና የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ፥ ካህኑ ያ ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ነገር ግን ቊስሉ ያለበት ስፍራ ምንም ለውጥ ሳያሳይና ሳይስፋፋ የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ በእሳት ቃጠሎ ምክንያት የመጣ ጠባሳ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት። “አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ቊስል ቢወጣበት ወይም ቢወጣባት፥ ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ በዙሪያው ካለው የሰውነት ቆዳ ይልቅ ወደ ውስጥ ጐድጒዶ በእርሱ ላይ የበቀለውም ጠጒር ወደ ቢጫነት በመለወጥ ስስ ሆኖ ከተገኘ የራስ ወይም የአገጭ ቈረቈር ወይም የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ነገር ግን ካህኑ ሲመረምረው የሚያሳክከው ቊስል በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ የማይታይ ከሆነና በላዩ ላይ ያለው ጠጒር ጤናማ ካልሆነ፥ በሚያሳክከው ቊስል ምክንያት ያ ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት ለሰባት ቀን እንዲቈይ ያድርግ፤ በሰባተኛው ቀን እንደገና ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ እየተስፋፋ ካልሄደ፥ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒርም ከሌለና በዙሪያው ካለው ከሌላው ሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘ፥ ያ ሰው ቊስሉን ሳይሆን በቊስሉ ዙሪያ ያለውን ጠጒር ይላጭ፤ ካህኑም እንደገና በሚያሳክከው በሽታ ምክንያት ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። በሰባተኛውም ቀን እንደገና ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ ቊስሉ በመስፋፋት ላይ ካልተገኘና በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ የጐደጐደ ካልሆነ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅለት፤ ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ሆኖም ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ቊስሉ እያመረቀዘ ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ በእርግጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ሰውየው የረከሰ በመሆኑ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒር መኖርና አለመኖሩ አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን በካህኑ አመለካከት ቊስሉ ካልተስፋፋና ጤናማ ጠጒርም በቅሎበት ከተገኘ፥ ቊስሉ የተፈወሰ ስለ ሆነ፥ ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት። “አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት በቈዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢወጣባቸው፥ ካህኑ ያን ሰው ይመርምር፤ ቋቁቻ ያለበትም ስፍራ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን ብዙ ጒዳት የማያመጣ በቈዳ ላይ የሚታይ ሽፍታ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ ነው። አንድ ሰው ጠጒሩ ከራሱ ላይ ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። አንድ ሰው ከግምባሩና ከዐናቱ ጠጒር ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። ነገር ግን በራ በሆነው ራስ ወይም ግንባር ላይ ወደ ቀይነት ያደላ ነጭ ቊስል ቢታይበት እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ በበራ ራሱ ወይም በበራ ግንባሩ ላይ በሰውነት ላይ የሚወጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ዐይነት ቀላ ያለ የእባጭ ቊስል ቢያገኝ፥ እርሱ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሰው በመሆኑ የረከሰ ነውና የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያውጅ፤ በሽታውም በራሱ ላይ ነው። “በዚህ ዐይነት የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበት ሰው የተቀዳደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጒሩን አያበጥር፥ ከንፈሩን ይሸፍን፤ ከዚያም በኋላ ‘እኔ የረከስኩ ነኝ! የረከስኩ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። ይህም በሽታ እስካለበት ድረስ ያ ሰው የረከሰ ይሆናል። ስለዚህም ከኅብረተሰብ ተለይቶ መኖሪያው ከሰፈር ውጪ ይሆናል። “ሻጋታ ነገር ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ በተሠራ ልብስ ቢወጣ፥ በድሩም ሆነ በማጉ ላይ፥ እንዲሁም ከሱፍ ወይም ከቈዳ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ ቢታይና፥ መልኩም ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት ቢያደላ፥ የሚተላለፍ ሻጋታ ስለ ሆነ ለካህኑ ይታይ። ካህኑም ይመርምረውና እነዚህ ሁሉ የልብስ ዐይነቶች እስከ ሰባት ቀን ድረስ በአንድ ክፍል ተዘግቶባቸው ይቈዩ። በሰባተኛውም ቀን እንደገና በሚመረምረው ጊዜ ሻጋታው ነገር ተስፋፍቶ ከታየበት ያ የታየው አጥፊ ሻጋታ ስለ ሆነ፥ የዚያ ዐይነቱ ልብስ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ይህም አጥፊ ሻጋታ እየሰፋ የሚሄድ ስለ ሆነ በእሳት ይቃጠል። “ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተስፋፍቶ ካልተገኘ፥ ልብሱ በውሃ ታጥቦ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለብቻ እንዲቀመጥ ያድርግ። ከዚህም በኋላ እንደገና ይመርምረው፤ ምንም እንኳ በማፋግ ባይስፋፋ የሻጋታው ቀለም ካልተለወጠ በቀር፥ አሁንም ርኩስ ነው፤ ከፊትም ሆነ ከኋላ ሻጋታ ወይም የመበስበስ መልክ የሚታይበት ያ ልብስ ይቃጠል። ነገር ግን ካህኑ እንደገና በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተቀንሶ ካገኘው፥ የመሻገት ምልክት ያለበትን ስፍራ ብቻ ከጨርቅ ወይም ከቈዳ ልብስ ቀዶ ያውጣው። ሻጋታው እንደገና ቢታይ እርሱ እየተስፋፋ የሚሄድ ስለ ሆነ፥ ባለ ንብረቱ ያቃጥለው። ልብሱ በሚታጠብበት ጊዜ የሻጋታው ምልክት ቢጠፋ እንደገና ይጠበው፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል።” ይህ እንግዲህ ከበፍታም ሆነ ከበግ ጠጒር፥ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ በድሩም ሆነ በማጉ በሻጋታ አማካይነት የሚተላለፍ ምልክት ተመርምሮ የሚታወቅበት የሥርዓት መመሪያ ነው።
ኦሪት ዘሌዋውያን 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 13:1-59
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች