እነሆ፥ ኢያሱ በዕድሜ እየገፋ ስለ ሄደ አረጀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፤ ዕድሜህም ገፍቶአል፤ ገና ብዙ ያልተያዙ ቦታዎች አሉ። ገና ያልተያዙትም እነዚህ ናቸው፦ የፍልስጥኤምና የገሹር ግዛት በሙሉ፥ እነዚህም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ካለው ከሺሆን ወንዝ ጀምሮ ወደ ሰሜን እስከ ኤክሮን ድንበር ድረስ ያለው ነው። ይህም በአጠቃላይ ከነዓን ተብሎ ይጠራል። እርሱም የአምስቱ የፍልስጥኤም ማለት የጋዛ፥ የአሽዶድ፥ የአስቀሎና፥ የጋትና የኤክሮን ነገሥታት ግዛት ነው። ሌሎች ያልተያዙ ደግሞ በደቡብ በኩል ያለው የአቢብ ግዛት ነው። በሌላም በኩል የሲዶናውያን ይዞታ የሆነው የከነዓን አገር መዓራ ተብሎ የሚጠራውን ሁሉ ጨምሮ በአሞራውያን ጠረፍ እስከ አፌቅ ድረስ የሚገኘው፥ የጌባላውያን ምድርና ከምሥራቅ በአርሞንኤም ተራራ ደቡብ ከሚገኘው ከባዓልጋድ ተነሥቶ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው መላው ሊባኖስ ገና አልተያዘም። ከሊባኖስ እስከ ሚስረፎትማይም ድረስ በተራራማው አገር የሚኖሩ ነዋሪዎች፥ ማለት ሲዶናውያንን ሁሉ፥ እኔ ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አባርራቸዋለሁ፤ አንተ ግን እኔ እንዳዘዝኩህ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ አከፋፍል። ይህንንም ምድር ርስት አድርገህ የምታካፍለው ለዘጠኙ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ነው።” የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በርስትነት የሰጣቸውን ምድር ቀደም ብለው ተረክበዋል። ይህም ምድር የሚገኘው በስተምሥራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ነው። ግዛታቸውም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ከሆነው ከዓሮዔር ተነሥቶ እንዲሁም በሸለቆው መካከል ካለው ከተማ ከሜዴባ ሜዳ እስከ ዲቦን ድረስ ይደርሳል። በሌላም በኩል በሓሴቦን እስከ አሞናውያን ድንበር ድረስ የነገሠውን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል። እርሱም ገለዓድን፥ የገሹርንና የማዕካን አውራጃዎችና የአርሞንኤምን ተራራ በሙሉ እንዲሁም እስከ ሳለካ ድረስ ያለውን ባሳንን ይጨምራል። ከራፋይማውያን ተራፊ የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የባሳንን ንጉሥ የዖግን መንግሥት ሁሉ ይጨምራል። ሙሴም እነዚህን ድል አድርጎ አስወጣቸው። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የገሹርንና የማዕካን ሕዝብ አላስወጡም፤ ነገር ግን እነርሱ እስከ አሁን በእስራኤላውያን መካከል ይኖራሉ። ሙሴ ለሌዊ ነገድ የርስት ድርሻ አልሰጠም፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በመሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ከሚቀርበው መባ የሚያገኙት ድርሻ እንደ ርስት ሆኖ ተመድቦላቸዋል።
መጽሐፈ ኢያሱ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 13:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች