እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚያን ጊዜ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ የእኔ የሆኑትን ሕዝቤን እስራኤልን በሕዝቦች መካከል ስለ በታተኑና ምድሪቱን ስለ ተካፈሉ በኢዮሣፍጥ ሸለቆ ወደ ፍርድ አቀርባቸዋለሁ። የማረኩአቸውን ሕዝቤንም ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጥለዋል፤ አመንዝራ ሴቶችን ለማግኘት ወንዶች ልጆችን ሰጡ፤ ወይን ጠጅ ለመጠጣትም ሴቶች ልጆችን ባሪያ አድርገው ሸጡ። “እናንተ የጢሮስ፥ የሲዶናና የፍልስጥኤም አውራጃዎች ሕዝብ ሆይ፥ ምን እያደረጋችሁ ነው? እኔን ለመበቀል ይቃጣችኋልን? ይህ ከሆነ ሥራችሁ ወዲያው በፍጥነት በራሳችሁ ላይ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ብሬንና ወርቄን እንዲሁም ውድ የሆነ ሀብቴን ሁሉ ወስዳችሁ ወደ ጣዖት ማምለኪያ ቤታችሁ አስገብታችኋል። የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ተወላጆች ከአገራቸው ድንበር አርቃችሁ በመውሰድ ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋል። እነሆ አሁን ከተሸጡባቸው ስፍራዎች አነሣሥቼ እንዲወጡ አደርጋለሁ፤ በእነርሱ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ በእናንተ ላይ መልሼ አመጣባችኋለሁ። የእናንተንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለይሁዳ ሕዝብ ተላልፈው እንዲሸጡ አደርጋለሁ፤ እነርሱም ሩቅ ላሉት ለሳባውያን ይሸጡአቸዋል፤ ይህንንም የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ይህን ለአሕዛብ ሁሉ ዐውጁ፤ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ጀግኖችን ቀስቅሱ፤ ጦረኞቻችሁ ሁሉ ተሰብስበው ለጦርነት ይሰለፉ። ማረሻችሁ ሰይፍ፥ ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡ፤ ደካማውም እንኳ ‘እኔ ብርቱ ነኝ’ ይበል፤ እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፤ በፍጥነት ውጡ! በሸለቆውም ተሰብሰቡ።” እግዚአብሔር ሆይ፥ ተዋጊ ሠራዊትህን ላክ። “አሕዛብ ሁሉ ተነሣሥተው ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ ይሂዱ፤ እኔ እግዚአብሔር በዙሪያ ባሉት አሕዛብ ላይ ለመፍረድ እዚያ እቀመጣለሁ። የእነርሱ ክፋት እጅግ በዝቶአል፤ የደረሰ መከር በማጭድ እንደሚታጨድ እጨዱአቸው፤ የወይን ዘለላ በመጥመቂያው ሞልቶ እንደሚረገጥ ርገጡአቸው፤” ጌታ በፍርድ ሸለቆ ፍርድ የሚሰጥበት ቀን ደርሶአል፤ ስለዚህ ቊጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ በዚያ ተሰብስቦአል። በዚያን ቀን ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ያጣሉ። እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በኢየሩሳሌም ሆኖ፥ የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤ ሰማይና ምድር ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ ለእስራኤል መጠጊያ ምሽግ ይሆናል፤ “እስራኤል ሆይ! በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ የባዕድ ወታደሮች አይወሩአትም። “በዚያን ጊዜ ተራራዎችም ሁሉ በወይን ተክል ይሸፈናሉ፤ በኰረብቶችም ላይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ከብቶች ይሰማራሉ፤ በይሁዳ ምድር የሚገኙ ወንዞች ሁሉ በውሃ የተሞሉ ይሆናሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ምንጭ ይፈልቃል፤ የሺጢምንም ሸለቆ ያጠጣል። “የግብጽና የኤዶም ሰዎች በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ስለ ፈጸሙና ንጹሑንም ሕዝብ ስለ ገደሉ፥ ‘ግብጽ ወደ በረሓነት ትለወጣለች፤ ኤዶምም ሰው የማይኖርባት ምድረ በዳ ትሆናለች።’ ስለዚህ እስከ አሁን ድረስ ሳልበቀልላቸው የቀረሁትን የንጹሐንን ደም እበቀላለሁ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ግን ለዘለዓለም ለሕዝቤ መኖሪያ ይሆናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ እኖራለሁ።”
ትንቢተ ኢዩኤል 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢዩኤል 3:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች