መጽሐፈ ኢዮብ 6:1-14

መጽሐፈ ኢዮብ 6:1-14 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በታየ ኖሮ! ከባሕር ዳር አሸዋ ይበልጥ በከበደ ነበር፤ ስለዚህ ትዕግሥት የጐደለው ንግግሬ ሊያስገርምህ አይገባም። ሁሉን የሚችል አምላክ በፍላጻዎቹ ወግቶኛል፤ መርዛቸውም በሰውነቴ ተሠራጭቶአል፤ የሚያስደነግጥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ዙሪያዬን ከቦኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ለምለም ሣር ካገኘ በሬም ድርቆሽ ካገኘ ይጮኻልን? ጨው ያልገባበት ጣዕም ያጣ ምግብ ይበላልን? የእንቊላልስ ውሃ ይጣፍጣልን? ለዚህ ዐይነቱ ምግብ ፍላጎት የለኝም፤ ብበላውም እንኳ ጤና ይነሣኛል። “ምነው እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ! ምነው ጸሎቴንስ በሰማኝ! ከዚህ ሁሉ ምነው ፈቃዱ ሆኖ ቢሰባብረኝ! እጁንም ሰንዝሮ ቢያጠፋኝ! ይህ ለእኔ መጽናናትን በሰጠኝ ነበር። የቅዱሱን ቃል ምንጊዜም ስላልካድኩ፥ ምንም እንኳ ሥቃይ ቢበዛብኝ በደስታ በዘለልኩ ነበር። በሕይወት ለመኖር የሚያበቃ ምን ብርታት አለኝ? ተስፋ ከሌለኝስ ለምን እኖራለሁ? እኔ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነኝን? ሰውነቴስ እንደ ናስ ጠንካራ ነውን? ራሴን ለመርዳት ምንም ኀይል የለኝም፤ ያለኝ ኀይል ሁሉ ተወስዶብኛል። “ለወዳጁ ያለውን ታማኝነት የሚነሣ ሰው እግዚአብሔርን መፍራቱን የተወ ነው።