የዮሐንስ ወንጌል 3:5-21

የዮሐንስ ወንጌል 3:5-21 አማ05

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው። ስለዚህ ‘ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል’ ስላልኩህ አትደነቅ። ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን? እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም። ምድራዊውን ነገር ስነግራችሁ የማታምኑ ከሆነ ሰማያዊውን ነገር ስነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። “ሙሴ በበረሓ እባብን ከፍ አድርጎ እንደ ሰቀለ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፍ ብሎ ሊሰቀል ይገባዋል። ይህም የሚሆነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲያገኝ ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደው አንድያ ልጁን ሰጠ። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው፥ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። “በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ቀድሞውኑ ተፈርዶበታል። “ፍርዱም ይህ ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ ክፉ ሥራውም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርግ ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ወደ ብርሃን የሚመጣውም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት መሆኑ በግልጥ እንዲታይ ነው።”