በቢታንያ የሚኖር አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ ቢታንያ ማርያምና እኅትዋ ማርታ የሚኖሩባት መንደር ነበረች። ይህች ማርያም የጌታን እግር ሽቶ የቀባችውና በጠጒርዋ ያበሰችው ናት፤ የታመመውም አልዓዛር የእርስዋ ወንድም ነበር። እኅትማማቾቹም “ጌታ ሆይ፥ ያ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ ኢየሱስ ላኩበት። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፥ “ይህ ሕመም ለሞት የሚያደርስ አይደለም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆንና የእግዚአብሔር ልጅም በዚህ ምክንያት እንዲከበር ነው” አለ። ኢየሱስ ማርታንና እኅትዋን ማርያምን ወንድማቸውን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። ሆኖም የአልዓዛርን መታመም በሰማ ጊዜ በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ወደ ይሁዳ ምድር እንደገና እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ ታዲያ እንደገና ወደዚያ ተመልሰህ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ያለው ጊዜ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ አይሰናከልም። ነገር ግን በሌሊት የሚመላለስ ብርሃን ስለሌለው ይሰናከላል።” ኢየሱስ ይህን ካላቸው በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፤ እኔ ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! አንቀላፍቶስ ከሆነ ይሻለዋል ማለት ነው” አሉት። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ስለ አልዓዛር መሞት ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በግልጥ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቶአል፤ እናንተ እንድታምኑ እዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ብሎኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።” በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት፥ “ከእርሱ ጋር እንድንሞት እኛም እንሂድ” አላቸው። ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም የምትርቀው ሦስት ኪሎ ሜትር ያኽል ነው። ከአይሁድም ብዙዎች ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ለማጽናናት ወደ እነርሱ መጥተው ነበር። ማርታ የኢየሱስን መምጣት በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፥ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ እንደገና ከሞት ይነሣል” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው።
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:1-32
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች