ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው የሚመጣው ለመስረቅ፥ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ቅጥረኛ እንጂ እውነተኛ ያልሆነ እረኛ ግን ተኲላ ሲመጣ በሚያይበት ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላውም በጎቹን ነጥቆ ይበታትናቸዋል። እረኛው የሚሸሸውም ቅጥረኛ ስለ ሆነና ለበጎቹም ስለማያስብ ነው። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” ከዚህ ንግግር የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎቹ፥ “እርሱ ጋኔን አለበት፤ አብዶአል፤ ስለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች “ይህ ንግግር ጋኔን ካለበት ሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ጋኔን የዕውርን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ወቅቱም ክረምት ነበር፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር። በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው፥ “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቈየናለህ? አንተ መሲሕ እንደ ሆንክ በግልጥ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። እነርሱን ለእኔ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ከአባቴ እጅ እነርሱን ነጥቆ መውሰድ የሚችል ማንም የለም። እኔና አብ አንድ ነን።” በዚህ ጊዜ አይሁድ ኢየሱስን ለመውገር እንደገና ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስም “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎችን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ፥ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ስለየትኛው ሥራ ነው?” አላቸው። እነርሱም “እኛ የምንወግርህ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ስለ መናገርህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህ አይደለም፤ ይኸውም አንተ ሰው ሆነህ ሳለ፥ ራስህን አምላክ ስላደረግህ ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “በሕጋችሁስ ‘እናንተ አማልክት ናችሁ አልኩ’ የሚል ተጽፎ የለምን? እንግዲህ ቅዱስ መጽሐፍን መሻር አይቻልም፤ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ቅዱስ መጽሐፍ አማልክት ብሎ ከጠራቸው ታዲያ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስለ አለ ስለምን ‘በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ትናገራለህ’ ትሉታላችሁ? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆንኩ አትመኑኝ። የአባቴን ሥራ የምሠራ ከሆንኩ ግን በእኔ እንኳ ባታምኑ በሥራዬ እመኑ፤ በዚህ ዐይነት አብ በእኔ እንደ ሆነና እኔም በአብ እንደ ሆንኩ በሚገባ ታውቃላችሁ።” እነርሱም እንደገና ሊይዙት ፈለጉ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አምልጦ ሄደ። እንደገናም ኢየሱስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ዮሐንስ መጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ቈየ። ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ ምንም ተአምር አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። እዚያም ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ።
የዮሐንስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 10:1-42
9 ቀናት
ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስረዳት ተግባራዊ እና የፈጠራ ታሪኮችን ተጠቅሟል። አንድ አጭር ቪዲዮ ዘጠኙን ክፍሎች ያሉት እቅድ በእያንዳንዱ ቀን ከኢየሱስ ትምህርቶች አንዱን ያሳያል።
ጌታ ኢየሱስ ስለ አገልግሎቱ ሲናገር ዓላማው ለሰዎች የዘላለም ሕይወት መስጠት እንደሆነ ተናግሯል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” (ዮሐ. 3፡16)። ይህ የዘላለም ሕይወት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የዘላለም ሕይወት ምን እንደሚል እንመልከት።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች