የዮሐንስ ወንጌል 10:1-11

የዮሐንስ ወንጌል 10:1-11 አማ05

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው የሚመጣው ለመስረቅ፥ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል።