ትንቢተ ኤርምያስ 52

52
የኢየሩሳሌም አወዳደቅ
(2ነገ. 24፥18-2025፥1-7)
1ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ የእናቱም ስም ሐሙጣል ይባል ነበር፤ እርስዋም የሊብናው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2ከዚያ በፊት ንጉሥ ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ ንጉሥ ሴዴቅያስም እግዚአብሔርን አሳዘነ። 3ስለዚህም እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ላይ ተቈጥቶ ከፊቱ አስወገዳቸው።
ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ 4ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በመምጣት በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል አስከበባት፤ ሠራዊቱም በከተማይቱም ዙሪያ ሰፈረ፤ በቅጥሩም ዙሪያ ዐፈር ቈለለ። #ሕዝ. 24፥2። 5ሴዴቅያስ እስከ ነገሠበት እስከ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ ከበቡአት። 6በዚያው ዓመት በአራተኛው ወር፥ በዘጠነኛው ቀን፥ ሕዝቡ የሚመገቡት አጥተው ራብ ጸና። 7የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ፤ ባቢሎናውያን ከተማይቱን ከበው ሳለ ወታደሮቹ በሌሊት አምልጠው ነበር፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ በሚወስደው መንገድ በኩል በማለፍ ሁለቱን ቅጽሮች በሚያገናኘው በቅጽር በር ወጥተው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ፤ #ሕዝ. 33፥21። 8ነገር ግን የባቢሎን ሠራዊት ሴዴቅያስን አሳዶ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ማረከው፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከድተውት ተበታተኑ። 9ሴዴቅያስም ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ተወሰደ፤ ናቡከደነፆር በዚያን ጊዜ በሐማት ግዛት ሪብላ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነበር፤ እዚያም ናቡከደነፆር በሴዴቅያስ ላይ የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈበት። 10ይኸውም በሪብላ ሴዴቅያስ ራሱ በዐይኑ እያየ ወንዶች ልጆቹ ተገደሉ፤ እንዲሁም የይሁዳን ባለ ሥልጣኖች አስገደለ። 11ከዚያም በኋላ የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ በእግር ብረት በማሰር ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እስከ ሞተበትም ጊዜ ድረስ በባቢሎን እስረኛ አደረገው። #ሕዝ. 12፥13።
የቤተ መቅደሱ መፍረስ
(2ነገ. 25፥8-17)
12ናቡከደነፆር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን የንጉሡ የክብር ዘብ አዛዥ የሆነው ናቡዛርዳን ኢየሩሳሌም ገባ፤ 13ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱንና በኢየሩሳሌም የነበሩ የታላላቅ ሰዎችን መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ታላላቅ ሕንጻዎችን አቃጠለ፤ #1ነገ. 9፥8። 14በክብር ዘቡ አዛዥ ይመራ የነበረው ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ቅጽር አፈራረሰ። 15የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዛርዳን ከሕዝቡ መካከል በጣም ድኻ የሆኑትን፥ በከተማ ውስጥ ቀርተው የነበሩትን፥ በመክዳት ወደ ባቢሎን ሠራዊት ተጠግተው የነበሩትንና ከእጅ ባለሙያዎች መካከል ቀርተው የነበሩትን ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 16ነገር ግን በይሁዳ የመጨረሻ ድኾች የነበሩትን ሕዝብ ተወ፤ እነርሱም የወይን ተክል ኰትኳቾችና አራሾች እንዲሆኑ አደረገ።
17ባቢሎናውያን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ ዐምዶችን፥ ተሽከርካሪ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና፥ ከነሐስ የተሠራውንም የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት። #1ነገ. 7፥15-47። 18ድስቶችን መሠዊያውን የሚያጸዱበትን የአካፋ ቅርጽ ያለውን መጫሪያውንና የዐመድ ማጠራቀሚያዎቹን ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ ጭልፋዎችንና ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ከነሐስ የተሠሩ ሌሎችንም ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ ወሰዱ። 19የክብር ዘቡ አዛዥ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ የዕጣን ማጠኛዎችን፥ ጐድጓዳ ወጭቶችን፥ ድስቶችን፥ መቅረዞችን፥ ጭልፋዎችን፥ የመጠጥ መሥዋዕት ማቅረቢያዎችን፥ በወርቅና በብር የተሠሩ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰደ።
20እንዲሁም ሁለቱን ምሰሶዎች፥ አንዱን ገንዳ፥ ዐሥራ ሁለት በኰርማ ቅርጽ ከነሐስ የተሠሩትን የገንዳ ማስቀመጫዎች፥ ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ አሠርቶአቸው የነበሩትን ተሽከርካሪ መቆሚያዎችን ሁሉ ወሰደ። እነዚህ ዕቃዎች የተሠሩበት ነሐስ ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ሊመዘን አልተቻለም። 21ሁለቱ ዐምዶች አንድ ዐይነት ቅርጽ ያላቸው ሆነው እያንዳንዳቸው ስምንት ሜትር ቁመትና አምስት ሜትር የሚያኽል ዙሪያ ነበራቸው፤ ውስጣቸውም ክፍት ነበር፤ ብረቱም ሰባ አምስት ሚሊ ሜትር ውፍረት ነበረው፤ 22የእያንዳንዱም ምሰሶ ጒልላት ከነሐስ የተሠራ ሆኖ ሁለት ሜትር ያኽል ከፍታ የነበረውና በመረብና በሮማን ፍሬ ቅርጽ የተጌጠ ነበር። 23በስተውጪ በኩል ዘጠና ስድስት የሮማን ፍሬ ቅርጾች የነበሩ ሲሆን በመረቡ ዙሪያ መቶ የሮማውያን ፍሬ ቅርጾች ነበሩ።
የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን መወሰዱ
(2ነገ. 25፥18-2127-30)
24ከዚያም ሁሉ ጋር የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዛርዳን ሊቀ ካህናቱን ሠራያን፥ በማዕርግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሌሎችንም ሦስት የቤተ መቅደስ በር ጠባቂዎችን አስሮ ወሰደ፤ 25ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነ አንድ ባለ ሥልጣንና እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ ውስጥ የተገኙትን ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች፥ የወታደራዊ ጉዳዮች ጸሐፊ የነበረውን የጦር አዛዡን ረዳትና ሌሎችንም ሥልሳ ታላላቅ ሰዎች ወሰደ፤ 26ናቡዛርዳን እነዚህን ሁሉ በሐማት ግዛት ውስጥ በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፤ 27ንጉሡም በዚያው አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው።
በዚህም ዐይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ፤ 28ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ብዛት ማስታወሻ ይህ ነው፤ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ የማረካቸው ሦስት ሺህ ኻያ ሦስት አይሁድ፥ 29በነገሠ በዐሥራ ስምንት ዓመቱ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፥ 30እንዲሁም በነገሠ በሃያ ሦስት ዓመቱ ሰባት መቶ አርባ አምስት አይሁድ በናቡዛርዳን እጅ ተማርከው ተወስደዋል፤ በጠቅላላው ተማርከው የተወሰዱት ሰዎች ቊጥር አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።
31የይሁዳ ንጉሥ ኢኮንያን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ አምስተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ኤዌል መሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከእስር ፈታው። 32ኤዊል መሮዳክ ኢኮንያንን በመልካም ሁኔታ አነጋገረው፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩት ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ቦታ ሰጠው። 33ስለዚህም ኢኮንያን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማዕድ ዘወትር እንዲመገብ ተፈቀደለት። 34በሚኖርበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር አበል ይሰጠው ነበር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ