ትንቢተ ኤርምያስ 46
46
እግዚአብሔር በግብጽ ላይ የፈረደው ፍርድ
1-2እግዚአብሔር ከግብጽ ጀምሮ ስለ መንግሥታት ሁሉ ተናገረኝ፤ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ካርከሚሽ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነኮ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ያዘመተውን ሠራዊት፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስለ ማድረጉ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ #ኢሳ. 19፥1-25፤ ሕዝ. 29፥1—32፥32።
3“ጋሻችሁን አዘጋጁ፤
ወደ ጦር ሜዳም ዝመቱ፤
4ፈረሶቻችሁን ለጒማችሁ ርካብ ረግጣችሁ ውጡ፤
የራስ ቊር ደፍታችሁ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤
ጦራችሁን ወልውሉ፤
የጦር ልብሳችሁንም ልበሱ።
5“ነገር ግን ይህ የማየው ነገር ምንድን ነው?
ከፍርሃት የተነሣ ወደ ኋላ በመመለስ ላይ ናቸው፤
ወታደሮቻቸው ድል ሆኑ፤
በየአቅጣጫው ፍርሀትና ሽብር ስላለ
ወደ ኋላ መለስ ብለው ሳያዩም ወደ ፊት ሸሹ።
6ነገር ግን ፈጣኖች እንኳ ሸሽተው አያመልጡም፤
ጐበዞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም፤ ከኤፍራጥስ በስተሰሜን በኩል ተሰናክለው ይወድቃሉ።
7ይህ እንደ ዓባይ ወንዝ የሚነሣና
ሞልቶ በጐርፉ ዳርቻውን ሁሉ
እንደሚያጥለቀልቅ ወንዝ የሆነ ይህ ማን ነው?
8እንደ ዓባይ ወንዝ የተነሣችውና
ሞልቶ በጐርፉ ዳርቻውን ሁሉ እንደሚያጥለቀልቅ ወንዝ የሆነችው ግብጽ ነች፤
ግብጽ እንዲህ ብላለች ‘እኔ ተነሥቼ ዓለምን አጥለቀልቃለሁ።
ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን ሕዝብ ሁሉ እደመስሳለሁ።’
9ፈረሶች ወደ ፊት እንዲሄዱ፥
ሠረገሎችም አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እንዲሽከረከሩ እዘዙ፤
ከኢትዮጵያና ከሊቢያ ጋሻቸውን አንግበው በመጡ ሰዎችና፥
ከልድያ በመጡ ቀስት በሚወረውሩ ኀያላን ሰዎች ጭምር
የተጠናከሩ ወታደሮችን ላኩ” ይላል እግዚአብሔር።
10ይህ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የመረጠው ቀን ነው፤
እርሱ ዛሬ የበቀል እርምጃ ይወስዳል፤
ጠላቶቹንም ይቀጣል።
የእርሱም ሰይፍ ብዙዎችን ይበላል፤
በደማቸውም ይለወሳል፤
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር
ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ሰሜን የሚገኙ ምርኮኞቹን መሥዋዕት ያደርጋቸዋል።
11እንደ ድንግል የምትታዪ ግብጽ ሆይ! ወደ ገለዓድ ሄደሽ
የሚቀባ መድኃኒት ፈልጊ፤
የአንቺ መድኃኒት ሁሉ ከንቱ ነው፤
ሊፈውስሽ የሚችል ነገር ከቶ የለም።
12ሕዝቦች ሁሉ ስለ ኀፍረትሽ ሰምተዋል፤
የዓለምም ሕዝብ ሁሉ ጩኸትሽን አድምጠዋል፤
አንዱ ወታደር ሌላውን ወታደር ሲያደናቅፈው ሁሉም ተያይዞ መሬት ይወድቃል።
የናቡከደነፆር አመጣጥ
13የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በግብጽ ላይ አደጋ ለመጣል ስለ መምጣቱ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ #ኤር. 43፥10-13።
14“የግብጽ ከተሞች በሆኑት በሚግዶል፥ በሜምፊስ
በጣፍናስ ይህን ቃል ዐውጅ፤
‘ራሳችሁን ለመከላከል ተዘጋጁ፤
በዙሪያችሁ ያለው ሁሉ በጦርነት ይጠፋል።
15ኀያል ነው የምትሉት አጲስ የተባለው ጣዖት ስለምን ወደቀ?
እግዚአብሔር ገፍቶ ስለ ጣለው አይደለምን?’
16ጀሌዎቻቸው ተሰናክለው አንዱ በአንዱ ላይ ይወድቃሉ፤
እርስ በርሱም አንዱ ሌላውን፥
‘ከጠላት ሰይፍ አምልጠን ከሀገራችን
ሕዝብ መቀላቀል እንድንችል እንፍጠን’ ይለዋል።”
17የግብጽን ንጉሥ “በዕድሉ የማይጠቀም ለፍላፊ፥” በሚል አዲስ ስም ይጠሩታል፤
18“ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ የሚጠራው ንጉሥ እንዲህ ይላል፦
“እኔ ሕያው ነኝ፤ በተራሮች መካከል ታቦር፥ በባሕር አጠገብ ቀርሜሎስ ከፍ ብለው እንደሚታዩ እንደዚሁ በእናንተ ላይ ከፍ ብሎ የሚታይ፥ ኀይል ይመጣል።
19የግብጽ ሕዝብ ሆይ! ተማርካችሁ የምትሄዱ ስለ ሆነ
ዕቃችሁን አዘጋጁ፤
ሜምፊስ ፈራርሳ ሰው የማይኖርባት በረሓ ትሆናለች፤
20ግብጽ እንደ ተዋበች ጊደር ናት፤
እርስዋ ከሰሜን በኩል በመጣ ተናካሽ ዝንብ ትወረራለች።
21ቅጥረኞች ወታደሮችዋም እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤
ወደ ኋላ ተመልሰው ይሸሻሉ፤
የፍርድና የጥፋት ቀን ስለ ደረሰባቸው፥
ጸንተው መዋጋት አይችሉም።
22-23የጠላት ሠራዊት ኀይል ሲቃረብ
ግብጽ እንደ እባብ የፉጨት ድምፅ እያሰማች ትሸሻለች፤
ሰዎች ጥቅጥቅ ያለውን ደን እንደሚመነጥሩ
በመጥረቢያ አደጋ ይጥሉባታል።
የሰዎቻቸው ብዛት በቊጥር አይደረስበትም፤
የወታደሮቻቸውም ብዛት ከአንበጣ ሠራዊት ይበልጣል፤
24የግብጽ ሕዝብ በሰሜን ሕዝብ ስለሚሸነፉ ያፍራሉ
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ግብጽን፥ አማልክትዋንና ነገሥታቶችዋን፥ የቴብስ አምላክ የሆነውን አሞንን፥ የግብጽን ንጉሥና በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ እቀጣለሁ። 26ሊገድሉአቸው ለሚፈልጉ ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ለሠራዊቱ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሆኖም ዘግየት ብሎ ከዚህ በፊት እንደሆነው ሁሉ ግብጽ እንደገና የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚታደግ
27“የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች
እስራኤላውያን ሆይ! አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤
እናንተን ከሩቅ አገር፥
ዘራችሁንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ።
እናንተም እንደገና ማንም ሳያስፈራችሁ
በሰላምና በደኅንነት ትኖራላችሁ። #ኤር. 30፥10-11።
28እኔ ከእናንተ ጋራ ስለ ሆንኩ አገልጋዮቼ እስራኤላውያን ሆይ!
እናንተ አትፍሩ፤
እናንተ በሀገራቸው እንድትበታተኑ
ያደረግኹባቸውን ሕዝቦች ሁሉ አጠፋለሁ፤
እናንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋችሁም፤
ሆኖም ለማረም እቀጣችኋለሁ፤
ሳልቀጣችሁ ግን አላልፍም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 46: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997