የሠራዊት አለቆች፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናንና የሆሻያ ልጅ ዐዛርያስ ሕዝቡም ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፦ “እባክህ የምንጠይቅህን ነገር አድርግልን! ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን! ከስደት ለተረፍነው ሁሉ ጸልይልን! ቀድሞ ብዙዎች ነበርን፤ አሁን ግን አንተ ራስህ እንደምታየን ጥቂቶች ብቻ ቀርተናል፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር በየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለብንና ምን ማድረግ እንደሚገባን ይገልጥልን ዘንድ ጸልይልን።” እኔም “መልካም ነው፤ ልክ እናንተ በጠየቃችሁት መሠረት ወደ እግዚአብሔር አምላካችሁ እጸልይላችኋለሁ፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ ከእናንተ ምንም ነገር ሳልሰውር እነግራችኋለሁ” ብዬ መለስኩላቸው። ከዚህም በኋላ እነርሱ እንዲህ አሉኝ “አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ አማካይነት የሚሰጠንን ትእዛዝ ሁሉ በመፈጸም ለቃሉ ታዛዦች ሆነን ባንገኝ፥ እርሱ ራሱ በእኛ ላይ እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁንብን! መልካም ቢሆንም ባይሆንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ቃል እንታዘዛለን፤ ወደ እርሱ የምንልክህም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብናከብር ሁሉ ነገር የሚሳካልን በመሆኑ ነው።” ከዐሥር ቀን በኋላ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ ስለዚህም ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊት አለቆች ሕዝቡንም ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወደ እኔ እንዲመጡ ጠራኋቸው፤ እንዲህም አልኳቸው፦ “ጥያቄአችሁን ወደ እርሱ እንዳቀርብ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህች ምድር የምትኖሩ ቢሆን እኔ እንደገና አንጻችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፤ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም፤ በእናንተ ላይ ያመጣሁት ጥፋት ታላቅ ሐዘን ሆኖብኛል፤ አሁን እንደምትፈሩት የባቢሎንን ንጉሥ ከእንግዲህ ወዲያ አትፍሩት፤ እኔ ከእናንተ ጋር ስለ ሆንኩ ከእርሱ ኀይል እታደጋችኋለሁ፤ እኔ እራራላችኋለሁ፤ እርሱም እንዲራራላችሁና ወደ አገራችሁ እንዲመልሳችሁ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’
ትንቢተ ኤርምያስ 42 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 42:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች