ትንቢተ ኤርምያስ 41
41
1በዚሁ ዓመት በሰባተኛው ወር ከንጉሡ ታላላቅ ባለ ሥልጣኖች አንዱ፥ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል የሆነውና የኤሊሻማዕ የልጅ ልጅ የነታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ አገረ ገዢውን ገዳልያን ለመጐብኘት ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ሁሉም በማዕድ ተቀምጠው አብረው ምግብ እየተመገቡ ሳሉ፥ 2እስማኤልና ዐሥሩ ሰዎች የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ላይ የሾመውን ገዳልያን በሰይፍ ገደሉት። 3እስማኤል በምጽጳ ከገዳልያ ጋር የነበሩትን አይሁድንና በዚያ ተገኝተው የነበሩትን የባቢሎናውያንን ወታደሮች ጭምር ፈጀ። #2ነገ. 25፥25።
4በማግስቱም ገዳልያ መሞቱን ማንም ሳያውቅ፥ 5ከሴኬም፥ ከሴሎና ከሰማርያ ሰማኒያ ሰዎች በድንገት መጡ፤ እነርሱም በሐዘን ጢማቸውን ላጭተው፥ ልብሳቸውን ቀደው፥ ፊታቸውን ነጭተው ነበር፤ ለቤተ መቅደስም መባ የሚያቀርቡትን እህልና ዕጣን ይዘው ነበር፤ 6ስለዚህም እስማኤል ከምጽጳ እያለቀሰ ሊቀበላቸው ወጣ፤ ወደ እነርሱም በቀረበ ጊዜ “የአሒቃም ልጅ ወደ ሆነው ወደ ገዳልያ ኑ” አላቸው። 7እነዚያም ሰዎች ከተማይቱ ውስጥ እንደ ገቡ የናታልያ ልጅ እስማኤልና ተከታዮቹ ገድለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው።
8ከእነዚያ ሰማኒያ ሰዎች መካከል በተለይ ዐሥሩ ሰዎች “እባክህ አትግደለን! እኛ በእርሻ ውስጥ የደበቅነው ብዙ ስንዴ፥ ገብስ፥ የወይራ ዘይትና ማር. አለን” ብለው እስማኤልን ለመኑት። እርሱም ምሕረት አደረገላቸው። 9እነዚያን ሰዎች ገድሎ የጣለበትም ያ ጒድጓድ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ አደጋ በጣለበት ጊዜ ንጉሥ አሳ ለመጠባበቂያ አስቈፍሮት የነበረ ትልቅ ጒድጓድ ነበር፤ እስማኤል ያን ጒድጓድ በሬሳ ሞላው። 10ከዚያም በኋላ የንጉሡን ሴቶች ልጆችና የቀሩትንም ሕዝብ በምጽጳ አሰረ፤ እነዚህም ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ ጦር አዛዥ ናቡዛርዳን በገዳልያ ሥር እንዲጠበቁ ዐደራ የተሰጡ ነበሩ፤ እስማኤል ግን እነዚህን ሁሉ ማርኮ ወደ ዐሞን ግዛት አቅጣጫ ተሻገረ።
11ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩት የሠራዊት መሪዎች ሁሉ እስማኤል የፈጸመውን ወንጀል ሰሙ፤ 12ስለዚህም ከሰዎቻቸው ሁሉ ጋር አሳደው ገባዖን ውስጥ ባለው ታላቅ ኲሬ አጠገብ ደረሱበት። 13እስማኤል አስሮ የወሰዳቸው ሁሉ ዮሐናንንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊቱን መሪዎች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14መለስ ብለውም በመሮጥ ከእነርሱ ጋር ተደባለቁ፤ 15እስማኤልና ስምንት ሰዎቹ ግን ከዮሐናን እጅ አምልጠው ወደ ዐሞን ምድር ኰበለሉ።
16ከዚህ በኋላ ዮሐናንና ከእርሱ ጋር ያሉት የሠራዊቱ መሪዎች፥ እስማኤል ገዳልያን ከገደለ በኋላ ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸውን ወታደሮች፥ ሴቶች፥ ሕፃናትና ጃንደረቦች ሁሉ መለሱ። 17-18እነርሱም የባቢሎን ንጉሥ ገዢ አድርጎ የሾመውን ገዳልያንን እስማኤል ስለ ገደለው ባቢሎናውያን አደጋ ያደርሱብናል ብለው ፈርተው ነበር፤ ስለዚህም ከባቢሎናውያን ፊት ሸሽተው ወደ ግብጽ ለመኰብለል ተነሡ፤ በቤተልሔም አጠገብ ባለችው ጌሩት ኪምሀም ተብላ በምትጠራው ቦታ ዕረፍት አደረጉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 41: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997