ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በምድያማውያን ምክንያት ችግር ደረሰባቸው፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እስራኤላውያን ከምድያማውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ሕዝብ አንድ ነቢይ ላከ፤ ያም ነቢይ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያመጣው መልእክት ይህ ነው፦ “እኔ በባርነት ከኖራችሁባት ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ከግብጻውያንና በዚህች ምድር ከሚጨቊኑአችሁ ሕዝቦች ሁሉ አዳንኳችሁ፤ ከፊታችሁም አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩና አሁን ምድራቸውን የወረሳችኋቸውን የአሞራውያንን ባዕዳን አማልክት እንዳታመልኩ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አልሰማችሁኝም።” ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው። ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው። እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው።
መጽሐፈ መሳፍንት 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 6:6-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች