ኦሪት ዘፍጥረት 4:10-26

ኦሪት ዘፍጥረት 4:10-26 አማ05

እግዚአብሔርም ቃየልን እንዲህ አለው፤ “ምን አደረግህ? የፈሰሰው የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው፤ የወንድምህን ደም ከአንተ ለመቀበል አፍዋን በከፈተችው ምድር ላይ የተረገምክ ነህ። ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ምንም ፍሬ አትሰጥህም፤ በምድር ላይም ስደተኛ ሆነህ ትንከራተታለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ይህ ቅጣት እኔ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፤ እነሆ፥ ዛሬ ከምድር አባረርከኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ስደተኛና ተንከራታች እሆናለሁ፤ እንግዲህ ማንም ሰው ቢያገኘኝ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን “ማንም አይነካህም፤ አንተን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ቃየልን ማንም ቢያገኘው እንዳይገድለው የሚያስጠነቅቅ ልዩ ምልክት አደረገለት። ከዚህ በኋላ ቃየል ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ ሄደ፤ በዔደን በስተምሥራቅ በሚገኘው በኖድ ምድር ኖረ። ቃየል ሚስቱን ከተገናኘ በኋላ ፀነሰች ሔኖክንም ወለደች፤ ቃየል ከተማን መሠረተ፤ በልጁም ስም “ሔኖክ” ብሎ ጠራት። ሔኖክ ዒራድን ወለደ፤ ዒራድ መሑያኤልን ወለደ፤ መሑያኤል መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤልም ላሜክን ወለደ፤ ላሜክ ዓዳ እና ጺላ የተባሉትን ሁለት ሚስቶች አገባ፤ ዓዳ ያባልን ወለደች፤ ያባልም ከብቶች እየጠበቁ በድንኳን ይኖሩ የነበሩት የዘላኖች ሰዎች አባት ነበረ። የእርሱ ወንድም ዮባልም ዋሽንትና በገና የሚጫወቱ የሙዚቀኞች አባት ነበር። ጺላም “ቱባልቃይን” የተባለ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሱ ከነሐስና ከብረት ልዩ ልዩ ዐይነት ዕቃዎችን ይሠራ ነበር። ቱባልቃይንም ናዕማ የተባለች እኅት ነበረችው። ላሜክ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ እናንተ “ዓዳ እና ጺላ የላሜክ ሚስቶች ሆይ፥ እስቲ አድምጡኝ፥ የምለውን ስሙ፤ አንድ ወጣት መትቶ ስላቈሰለኝ ገደልኩት፤ ቃየልን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል ከተባለ፥ እኔን የሚገድል ደግሞ ሰባ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።” አዳምና ሔዋን ሲገናኙ እንደገና ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እርስዋም “ቃየል በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ወንድ ልጅ ሰጠኝ” ስትል “ሤት” የሚል ስም አወጣችለት። ሤትም “ሄኖስ” የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመሩት በዚያን ጊዜ ነው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}