ኦሪት ዘፍጥረት 26:12-35

ኦሪት ዘፍጥረት 26:12-35 አማ05

ይስሐቅ በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ እግዚአብሔር ስለ ባረከውም በዚያኑ ዓመት መቶ እጥፍ አመረተ፤ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ስለ ሄደ እጅግ ባለጸጋ ሆነ። ብዙ የበግና የከብት መንጋ፥ እንዲሁም ብዙ አገልጋዮች ስለ ነበሩት ፍልስጥኤማውያን ቀኑበት። ስለዚህ የይስሐቅ አባት አብርሃም በሕይወት በነበረበት ዘመን የእርሱ አገልጋዮች ቆፍረዋቸው የነበሩትን የውሃ ጒድጓዶች ሁሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑአቸው። በዚያን ጊዜ አቤሜሌክ ይስሐቅን “ኀይልህ ከእኛ ይልቅ እየበረታ ስለ ሄደ፥ አገራችንን ለቀህ ውጣ” አለው። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ያንን ቦታ ለቆ በገራር ሸለቆ ውስጥ ሰፈረ፤ እዚያም ተቀመጠ። አብርሃም በሕይወት ሳለ አስቈፍሮአቸው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ግን ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች ይስሐቅ እንደገና እንዲቈፈሩ አደረገ፤ አባቱ ባወጣላቸው ስሞችም ጠራቸው። የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ የውሃ ጒድጓድ ቆፈሩና ጥሩ የምንጭ ውሃ አገኙ፤ የገራር እረኞች ግን “ይህ ውሃ የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ተጣሉ። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ጒድጓዱን “ዔሤቅ” ብሎ ሰየመው። የይስሐቅ አገልጋዮች ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ በዚህኛውም ጒድጓድ ምክንያት ሌላ ጠብ ተነሣ፤ ስለዚህ ይስሐቅ ይህን ጒድጓድ “ስጥና” ብሎ ሰየመው። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈረ፤ በዚህኛው የውሃ ጒድጓድ ምክንያት ምንም ጠብ ስላልተነሣ “እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጠን፤ በምድር ላይም እንበዛለን ሲል፥ ያንን ቦታ ‘ረሖቦት’ ” ብሎ ሰየመው። ከዚህ በኋላ ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ፤ በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍራ፤ ለአገልጋዬ ለአብርሃም በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ” አለው። ይስሐቅ በዚያ መሠዊያ ሠራና ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ መኖሪያውንም እዚያ አደረገ፤ አገልጋዮቹም ሌላ ጒድጓድ ቈፈሩ። አቤሜሌክ ከአማካሪው ከአሑዘትና ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ይስሐቅን ለመጐብኘት ከገራር መጣ፤ ስለዚህ ይስሐቅ “ከዚህ በፊት ጠልታችሁኝ ከአገራችሁ እንድወጣ አድርጋችሁኛል፤ ታዲያ አሁን ልትጐበኙኝ የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጥ ዐውቀናል፤ ስለዚህ በእኛና በአንተ መካከል በሰላም ለመኖር የሚያስችል ስምምነት በመሐላ ለመፈጸም አስበናል፤ በዚህም መሠረት ቃል ኪዳን እንድትገባልን የምንፈልገው፥ እኛ በአንተ ላይ ምንም ግፍ እንዳልሠራን አንተም በእኛ ላይ ምንም ዐይነት በደል እንዳታደርስብን ነው፤ ዘወትር መልካም ነገር አደረግንልህ እንጂ ክፉ አላደረግንብህም፤ ከአገራችንም የወጣኸው በሰላም ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ባርኮሃል።” ከዚህ በኋላ፥ ይስሐቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ጠጡ። በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሡና ተማማሉ፤ ይስሐቅ ካሰናበታቸው በኋላም በሰላም ሄዱ። በዚያኑ ቀን የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቆፈሩት ጒድጓድ ለይስሐቅ ነገሩት፤ “ውሃ አገኘን” ብለውም ነገሩት። እርሱም የውሃውን ጒድጓድ “ሳቤህ” ብሎ ጠራው፤ ስለዚህም የከተማይቱ ስም እስከ ዛሬ “ቤርሳቤህ” እየተባለ ይጠራል። ዔሳው አርባ ዓመት ሲሆነው የብኤሪን ልጅ ዮዲትንና የኤሎንን ልጅ ባሴማትን አገባ፤ ሁለቱም ሒታውያን ነበሩ። ይህም ጋብቻ ይስሐቅንና ርብቃን ሲያሳዝናቸው ይኖር ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}