ከዚህ በኋላ ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ወዳጩአቸው ሰዎች ቤት ሄደና “ቶሎ ብላችሁ ከዚህ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህን ስፍራ ሊደመስሰው ነው” አላቸው፤ እነርሱ ግን የሚቀልድ መስሎአቸው ቸል አሉ። በማግስቱ ጠዋት በማለዳ መላእክቱ ሎጥን “ፍጠን! ከተማይቱ ስትጠፋ አብራችሁ እንዳትጠፉ ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ውጣ” እያሉ አጣደፉት። ሎጥ ግን አመነታ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእርሱና ለቤተሰቡ ስለ ራራ መላእክቱ ሎጥንና ሚስቱን፥ ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፥ እጆቻቸውን ይዘው ከከተማዋ እንዲያወጡአቸው አደረገ። ካወጡአቸውም በኋላ ከመላእክቱ አንዱ “ሕይወታችሁን አድኑ! ወደ ኋላ አትመልከቱ! በሸለቆው ውስጥ አትዘግዩ፤ እንዳትሞቱ ወደ ተራራው ሽሹ!” አላቸው። ሎጥ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ፥ እባካችሁ ወደዚያ እንድንወጣ አታደርጉ፤ እኔ አገልጋያችሁ በፊታችሁ ሞገስ ስላገኘሁ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርዳታ አድርጋችሁልኛል፤ ነገር ግን ይህ ጥፋት ደርሶብኝ እሞታለሁ ብዬ ስለምሰጋ ወደዚያ ተራራ መሸሽ አልችልም። እኔ በፍጥነት ሸሽቼ ላመልጥበት የምችል እነሆ አንዲት ትንሽ ከተማ በቅርብ አለች፤ ስለዚህ ሸሽቼ ወደ እርሷ እንድሄድ ፍቀዱልኝ፤ እንደምታዩአት ትንሽ ከተማ ናት፤ ወደ እርስዋ ብሄድ ሕይወቴ ከጥፋት ይድናል።” መልአኩም “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ ይህችን አንተ የምትላትን ከተማ አላጠፋትም፤ ወደዚያች ከተማ እስከምትደርስ ምንም ማድረግ ስለማልችል ፈጥነህ ወደ እርስዋ ሽሽ!” አለው። ሎጥ ያቺን ከተማ ትንሽ ብሎአት ስለ ነበር ጾዓር ተባለች። ሎጥ ወደ ጾዓር ሲደርስ ገና ፀሐይ መውጣትዋ ነበር፤ እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን ከራሱ (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ከሰማይ አዘነበ። በዚህ ዐይነት እነዚያን ከተሞችና ሸለቆዎች፥ እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፥ በምድሩም ላይ የበቀለውን ነገር ሁሉ ደመሰሰ። የሎጥ ሚስትም ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች።
ኦሪት ዘፍጥረት 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 19:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች