ኦሪት ዘፍጥረት 18:1-33

ኦሪት ዘፍጥረት 18:1-33 አማ05

በመምሬ የወርካ ዛፎች አጠገብ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት፤ የተገለጠለትም በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ከዕለታት አንድ ቀን በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ነበር፤ ቀና ብሎም ሲመለከት ሦስት ሰዎች እዚያ ቆመው አየ፤ እንዳያቸውም ወዲያውኑ ሊያነጋግራቸው ወደ እነርሱ ሮጠ፤ ግንባሩም መሬት እስኪነካ ዝቅ ብሎ በመስገድ እጅ ነሣ፤ እንዲህም አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አልፈኸኝ እንዳትሄድ እለምንሃለሁ፤ እግራችሁን የምትታጠቡበት ውሃ እስካመጣላችሁ ድረስ በዚህ ዛፍ ጥላ ሥር ዐረፍ በሉ፤ ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ በመምጣታችሁ ደስ ብሎኛል፤ ስለዚህ ለጒዞአችሁ ብርታት የሚሰጣችሁን ጥቂት ምግብ አምጥቼ እንዳስተናግዳችሁ ፍቀዱልኝ።” እነርሱም “መልካም ነው፤ እንዳልከው አድርግ” አሉት። አብርሃም ወደ ድንኳኑ ሮጦ ሄደና ሣራን “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውሰጂና አቡክተሽ እንጀራ ጋግሪ” አላት። ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ መንጋው ሄደና ለግላጋውንና መልካሙን ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም በፍጥነት ዐርዶ አወራርዶ አዘጋጀው፤ አብርሃም እርጎ፥ ወተትና ሥጋ ይዞ ሄደና ምግቡን ለእንግዶቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱ ምግቡን በሚበሉበት ጊዜ አብርሃም ከዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ያስተናግዳቸው ነበር። እነርሱም “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” አሉት። እርሱም “እዚያ ድንኳኑ ውስጥ ነች” አላቸው። ከሦስቱም እንግዶች አንዱ አብርሃምን “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። እርሱም ይህን በሚናገርበት ጊዜ ሣራ በስተኋላው በድንኳኑ ደጃፍ ቆማ ታዳምጥ ነበር፤ አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው መግፋት አርጅተው ነበር፤ የሣራም፥ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ ነበር። ስለዚህ ሣራ “እኔ አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ጌታዬ አብርሃምም ካረጀ በኋላ እንዲህ ያለ ደስታ ሊኖረኝ ይችላልን?” ብላ በማሰብ ሳቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ‘እንደዚህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁን’ በማለት ስለምን ሳቀች? ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እንደ ነገርኩህ የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። ሣራ እጅግ ፈርታ ስለ ነበር “አልሳቅሁም” ብላ ካደች። እርሱ ግን “በእርግጥ ስቀሻል” አላት። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ለመሄድ ተነሡ፤ ሰዶምን ቊልቊል ወደሚያዩበት ስፍራም ደረሱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውረዋለሁን? የአብርሃም ዘር ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ በእርሱም አማካይነት በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ። ቅንና ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ እንዲጠብቁ ልጆቹንና ቤተሰቡን በመምከር ይመራቸው ዘንድ እኔ እርሱን መርጬዋለሁ፤ ልጆቹ ይህን ካደረጉ እኔም ለአብርሃም የሰጠሁትን ተስፋ ሁሉ እፈጽማለሁ።” ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “የሰዶምና የገሞራ ሕዝብ የሚፈጽሙት በደል ምን ያኽል እንደ ሆነ ሰምቼአለሁ፤ ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ መሆን አለበት፤ ስለ እነርሱ የሰማሁት ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ እነርሱ እወርዳለሁ።” ከዚህ በኋላ ሁለቱ ሰዎች ወደ ሰዶም ለመሄድ ተነሡ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ቈየ፤ ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ በደል የሌለባቸውን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህን? በከተማይቱ ውስጥ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ቢገኙ ከተማይቱን በሙሉ ትደመስሳለህን? ስለ ኀምሳው ደጋግ ሰዎች ስትል ከተማይቱ እንዳትጠፋ አታደርግምን? በደል ያልሠሩትን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህ ብዬ አላስብም፤ ይህንን እንደማታደርገው አምናለሁ፤ ይህንንማ ካደረግህ ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር መቀጣታቸው ነው፤ ይህ ከቶ አይሆንም! የዓለም ሁሉ ፈራጅ በትክክል መፍረድ ይገባው የለምን?” እግዚአብሔርም “በሰዶም ከተማ ውስጥ በደል ያልሠሩ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ባገኝ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን ፈጽሞ አላጠፋም” አለ። አብርሃም እንደገና እንዲህ አለ፤ “እኔ ትቢያና ዐመድ የሆንኩ ከንቱ ሰው፥ ከጌታዬ ጋር በድፍረት በመነጋገሬ ይቅር በለኝ፤ ነገር ግን የደጋግ ሰዎች ቊጥር ኀምሳ መሆኑ ቀርቶ አርባ አምስት ቢሆን፥ አምስት ስለ ጐደለ ከተማይቱን በሙሉ ታጠፋለህን?” እግዚአብሔርም “አርባ አምስት ደጋግ ሰዎች ባገኝ ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “አርባ ብቻ እዚያ ቢገኙስ?” ብሎ እንደገና ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አርባ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ፤ እንደገና ልናገር፤ ምናልባት ሠላሳ ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እግዚአብሔርም “ሠላሳ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ አሁንም እንደገና በመናገሬ ይቅር በለኝ፤ ምናልባት ኻያ ቢገኙስ?” አለ፤ እግዚአብሔርም “ኻያ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ አንድ ጊዜ ልናገር፤ ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እግዚአብሔርም “ዐሥር ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ካበቃ በኋላ ከዚያ ስፍራ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}