ትንቢተ ሕዝቅኤል 3:1-15

ትንቢተ ሕዝቅኤል 3:1-15 አማ05

እግዚአብሔርም “የሰው ልጅ ሆይ! የቀረበልህን ብላ፥ ይህን የብራና ጥቅል ብላ፤ ወደ እስራኤልም ሕዝብ ሄደህ ተናገር!” አለኝ። ስለዚህ አፌን ከፈትኩ፤ የብራናውንም ጥቅል እንድበላው ሰጠኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን የሰጠሁህን የብራና ጥቅል ብላው! ሆድህንም በእርሱ ሙላው!” አለኝ፤ እኔም በበላሁት ጊዜ ጣፋጭነቱ እንደ ማር. ነበር። ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄደህ እኔ የምነግርህን ቃል ንገራቸው፤ እኔ የምልክህ ወደ እስራኤላውያን እንጂ ቋንቋቸው ወደማይታወቅ ባዕዳን ሕዝብ አይደለም፤ ንግግራቸው ግራ የሚያጋባ፥ ቋንቋቸው ወደማይታወቅና የቃላቸውን ትርጒም ልታስተውለው ወደማትችል ታላላቅ ሕዝቦች ልኬህ ቢሆን ኖሮማ በሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ እኔን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ አንተንም አይሰሙህም። እኔ ግን አንተን እንደ እነርሱ እልኸኛና የማትበገር አደርግሃለሁ። አንዳችም የሚገታህ ነገር እስከማይኖር ድረስ መልእክቴን ለመናገር ቈራጥ ትሆናለህ፤ አንተን ይበልጥ ያጠነከርኩህ ስለ ሆነ እነዚህን በዕብሪት ዐመፀኞች የሆኑትን የምትፈራበት ምንም ምክንያት የለም።” ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምናገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠህ አስብበት። በምርኮ ወደሚገኙት የአገርህ ሕዝብ ሄደህ ቢሰሙህም ባይሰሙህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ ንገራቸው።” ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አደረገኝ፤ ከበስተኋላዬም “በሰማይ ለሚኖር እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይሁን!” የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። የሕያዋን ፍጥረቶቹ ክንፎቹ እርስ በርሳቸው በአየር ላይ ሲፋጩ ሰማሁ፤ ከመንኰራኲሮቹም የሚሰማው የጋጋታ ድምፅ ከፍተኛ ነበር። መንፈስ አንሥቶ በወሰደኝ ጊዜ ስሜቴ በምሬትና በቊጣ ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ኀይል በእኔ ላይ በርትቶ ነበር። ስለዚህ በኬባር ወንዝ አጠገብ ወዳለው ወደ ቴል አቢብ መጣሁ፤ ይህም ስፍራ የምርኮኞች መኖሪያ ነበር፤ ባየሁትና በሰማሁት ነገር ሁሉ በመደንገጥ ደንዝዤ በመካከላቸው ሰባት ቀን ቈየሁ።