ትንቢተ ሕዝቅኤል 20:1-38

ትንቢተ ሕዝቅኤል 20:1-38 አማ05

በተሰደድን በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ጥቂቶቹ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊጠይቁኝ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ለእነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፥ ‘ፈቃዴን ለማወቅ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው እንደ መሆኔ ምንም ነገር እንድትጠይቁኝ አልፈቅድላችሁም፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ “የሰው ልጅ ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ ትፈርድባቸዋለህን? ትፈርድባቸዋለህን? እንግዲያውስ አባቶቻቸው ያደረጉትን አጸያፊ ነገር እንዲያውቁ አድርጋቸው። እንዲህም በላቸው፦ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን በመረጥኩ ጊዜ ለያዕቆብ ዘር በግብጽ ምድር ራሴን በማሳወቅ ቃል ገባሁላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኳቸው። ከግብጽ ምድር አወጣኋቸው፤ ለእነርሱ የመረጥኩላቸው ምድር በማርና በወተት የበለጸገች ነበረች፤ እርስዋም ከዓለም ምድር ሁሉ ይበልጥ የተዋበች ነበረች፤ ወደዚያች ምድርም እንደማስገባቸው ቃል የገባሁላቸው በዚያን ጊዜ ነው። እንዲህም አልኳቸው፦ ‘እያንዳንዳችሁ የምታተኲሩባቸውን አጸያፊ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖቶችም ራሳችሁን አታርክሱ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።’ ነገር ግን እነርሱ ዐመፀኞች ሆኑ እንጂ እኔን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ዐይኖቻቸው ያተኰሩባቸውን አጸያፊ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖት ማምለክ አልተዉም፤ ስለዚህ በግብጽ በነበሩበት ጊዜ ቊጣዬን ላወርድባቸው አስቤ ነበር። ነገር ግን አብረዋቸው በሚኖሩት ሕዝቦች ፊት ከግብጽ እንደማወጣቸው ለእስራኤላውያን ቃል ገብቼ ነበር፤ ስለዚህ ስሜ እንዳይነቀፍ እነርሱን ከግብጽ እንዲወጡ አድርጌአለሁ። “ስለዚህም ከግብጽ መርቼ ወደ በረሓ አመጣኋቸው፤ ለሚታዘዘው ሁሉ በሕይወት መኖር የሚችልበትን ሕጌን ሰጠኋቸው፤ ሥርዓቴንም አስተማርኳቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ መሆኔን ያውቁ ዘንድ ሰንበትን ማክበራቸው በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት እንዲሆን አደረግሁ። ነገር ግን እስራኤላውያን በበረሓ ሳሉ እንኳ በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚያስገኝለትን ሕጌንና ሥርዓቴን ጣሱ፤ ፈጽመውም ሰንበትን አረከሱ፤ በዚያም በበረሓ ቊጣዬን በእነርሱ ላይ በመግለጥ ላጠፋቸው አስቤ ነበር፤ ነገር ግን እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር መርቼ ሳወጣ በተመለከቱኝ ሕዝቦች ፊት ስሜ እንዳይነቀፍ ይህን ሁሉ አላደረግሁም። ከዚህም በላይ ከዓለም ምድር ሁሉ ውብ የሆነችውንና በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እሰጣችኋለሁ ብዬ ቃል ገብቼላቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በበረሓ እያሉ ወደዚያ እንደማላስገባቸው አረጋግጬ ነገርኳቸው። ይህንንም ውሳኔ ያደረግኹበት ምክንያት ልባቸው ወደ ጣዖቶቻቸው በማምራት ሕጌንና ሥርዓቴን ስላፈረሱ፥ ሰንበትንም ስላረከሱ ነው።” ይህም ሆኖ ስለ ራራሁላቸው አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልጨረስኳቸውም። ለልጆቻቸውም እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፦ “የቀድሞ አባቶቻችሁ ባወጡት ድንጋጌ አትመሩ፤ ሥርዓታቸውንም አትከተሉ፤ ወይም በጣዖቶቻቸው አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ ለሕጌም በጥንቃቄ ታዘዙ። እኔ ከእናንተ ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን ምልክት ይሆንላችሁ ዘንድ፥ እንዲሁም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ያስታውሳችሁ ዘንድ ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርጉት። “ነገር ግን ልጆቻቸው በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ለሚፈጽመው ሁሉ ሕይወት የሚያስገኝለትን ሕጌን አፈረሱ፤ ሕጎቼንም አልጠበቁም፤ ሰንበትንም አረከሱ፤ በዚያም በበረሓ ሳሉ የቊጣዬን ኀይል በእነርሱ ላይ በማውረድ ሁሉንም ላጠፋቸው አስቤ ነበር። ነገር ግን እስራኤላውያንን ከግብጽ ማውጣቴን በተመለከቱ ሕዝቦች ዘንድ ስሜ እንዳይነቀፍ ይህን አላደረግሁም። ከዚህም በላይ በተለያዩ አገሮች በሕዝቦች መካከል እንደምበታትናቸው በምድረ በዳ እያሉ በመሐላ አረጋግጬ ነገርኳቸው። ይህንንም ያደረግኹት ሕጌን ስለ ተላለፉ፥ ሥርዓቴንም ስላልተከተሉ፥ ሰንበትን ስላረከሱ፥ የቀድሞ አባቶቻቸውንም ጣዖቶች ስለ አመለኩ ነው። “ከዚህ በኋላ መልካም ያልሆነውን ሕግና ሊኖሩበት ያልቻሉትን ሥርዓት ሰጠኋቸው። የበኲር ልጆቻቸውን እስከ መሠዋት ድረስ ተቀባይነት የሌለውን መሥዋዕት በማቅረብ ራሳቸውን እንዲያረክሱ ተውኳቸው፤ ይህንንም ያደረግኹት እነርሱን መቀጣጫ የማደርጋቸው እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቁ ዘንድ ነው። “እንግዲህ የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ አባቶቻቸው እኔን በመካድ በዚህ ተዳፈሩኝ። ለእነርሱ እንደምሰጣቸው ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር አመጣኋቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱ ከፍተኛ ኰረብቶችንና ለምለም ዛፎችን ባዩ ጊዜ በሁሉም ላይ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በሚቃጠል መሥዋዕታቸው፥ መዓዛው በሚጣፍጥ ዕጣናቸውና ለመሥዋዕትም በሚያፈሱት የመጠጥ ቊርባናቸው አስቈጡኝ፤ እኔም ‘እነዚህ የምትሄዱባቸው ከፍተኛ ቦታዎች ምንድን ናቸው?’ ብዬ ጠየቅኋቸው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ‘ከፍተኛ ቦታዎች’ ተብለው ይጠራሉ። አሁንም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንደ አባቶቻችሁ ራሳችሁን በማርከስና የእነርሱን አጸያፊ ጣዖቶች በማምለክ ለምን ትስታላችሁ? ዛሬም እንኳ ተመሳሳይ መባ ታቀርባላችሁ፤ ልጆቻችሁን በእሳት ውስጥ መሥዋዕት አድርጋችሁ በማቅረብ በእነዚያው በጥንታውያኑ ጣዖቶች ራሳችሁን ታረክሳላችሁ፤ ይህን ሁሉ ካደረጋችሁ በኋላ እናንተ እስራኤላውያን ፈቃዴ ምን እንደ ሆነ ለመጠየቅ ትመጣላችሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር በእርግጥ ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ ምንም ነገር እንድትጠይቁኝ አልፈቅድላችሁም! እንደ ሌሎች ሕዝቦች ወይም ለዛፍና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ በሌሎች አገሮች እንደሚኖሩ አሕዛብ ለመሆን ወስናችኋል፤ ነገር ግን ይህ ከቶ ሊሆን አይችልም።’ ” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ በእርግጥ በሥልጣኔ፥ በሙሉ ኀይሌና በቊጣዬ በእናንተ ላይ እነግሣለሁ። ከተበታተናችሁባቸው አገሮችና ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ የምሰበስባችሁም በኀይሌና ሥልጣኔ፥ በማወርደው ቊጣዬ ነው። ‘የሕዝቦች በረሓ’ ተብላ ወደምትጠራ ምድር አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ዐይናችሁ እያየ እፈርድባችኋለሁ፤ በግብጽ በረሓ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ፈረድኩ በእናንተም ላይ እፈርዳለሁ፤” ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። “ከሥልጣኔ ሥር አደርጋችኋለሁ፤ ወደ ቃል ኪዳኔ ግዴታም አመጣችኋለሁ። ዐመፀኞችንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ አሁን ከሚኖሩባቸው አገሮች አወጣቸዋለሁ፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ምድር እንዲመለሱ ከቶ አልፈቅድላቸውም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”