ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ለእግዚአብሔር መባ አቅርቡ፤ መባ ለማቅረብ የፈለገ ሁሉ እያንዳንዱ ልቡ የፈቀደውን ያኽል የወርቅ፥ የብር፥ ወይም የነሐስ ጥሩ ከፈይ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ቀለም የተነከረ የበግ ጠጒር፥ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ የለፋ ቊርበት፥ የግራር እንጨት፥ ለመብራት የሚሆን የወይራ ዘይት፥ ለቅባት ዘይትና ለዕጣን ሽታ የሚሆን ቅመማ ቅመም፥ በተቀደሰው ኤፉድና የደረት ኪስ ላይ የሚሆን መረግድና ሌላውንም ጌጠኛ ፈርጥ ያምጣ። “በመካከላችሁ የሚገኙ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ እግዚአብሔር ያዘዘውን ማናቸውንም ነገር ለመሥራት ይምጡ፤ ይኸውም ድንኳኑን፥ የውስጥና የውጪ መደረቢያዎችን፥ መያዣዎችንና ተራዳዎችን መወርወሪያዎችንና ምሰሶዎችን፥ እግሮቹን፥ የኪዳኑን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውንና የታቦቱ መሸፈኛ የሆነውን መጋረጃ፥ ጠረጴዛውን፥ መሎጊያዎቹንና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የተቀደሰ ኅብስት ለመብራት ማኖሪያ የሚሆነውን መቅረዝና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች፥ መብራቶቹም ከዘይታቸው ጋር፥ የዕጣን መሠዊያውንና መሎጊያዎቹን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፥ የድንኳኑን በር መጋረጃ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ፥ የነሐሱንም መከላከያ መሎጊያዎቹንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን፥ ያደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹንና እግሮቻቸውን፥ የአደባባዩን በር መጋረጃዎች፥ የድንኳኑንና የአደባባዩን ካስማዎች፥ አውታሮችና ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚያገለግሉበት ጊዜ የሚለብሱአቸው በጥበብ ያጌጡ ልብሶችን ይኸውም ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ የተሠሩትን የተቀደሱ ልብሶች ይሥሩ።” ከዚህ በኋላም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤ ለመሥራት እያንዳንዱ ለመስጠት ልቡ የፈቀደውን ለእግዚአብሔር መባ አመጣ፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለካህናት ልብስ የሚሆነውን ነገር ሁሉ አመጡ። ስጦታ ማቅረብ የፈለገ ሴቱም ወንዱም እያንዳንዱ የደረት ጌጥ፥ የጆሮ ወርቅ፥ የጣት ቀለበት፥ ድሪዎችና የወርቅ ጌጦችን አምጥቶ ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ አደረገ። ጥሩ በፍታ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ እንዲሁም የለፋ ቊርበት ያለው ሁሉ ይዞ መጣ። ብር ወይም ነሐስ ለማቅረብ ችሎታ ያላቸውም ሁሉ ስጦታቸውን ለእግዚአብሔር አመጡ፤ ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል የግራር እንጨት ያለውም አመጣ። የእጅ ጥበብ ችሎታ ያላቸው ሴቶችም በእጃቸው የሠሩትን ጥሩ በፍታና ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ስጦታ ለማቅረብ የፈለጉ ሴቶች ከፍየል ጠጒር የተገመደ ክር ሠሩ፤ አለቆችም በተቀደሰው ኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግድና ሌሎችም ጌጣጌጦች፥ ለመብራትና ለቅባት እንዲሁም ጣፋጭ ሽታ ለሚሰጥ ዕጣን የሚሆን ቅመማ ቅመምና ዘይት አመጡ፤ ወንዶችና ሴቶች የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ላዘዘው ሥራ የሚውል ልባቸው የፈቀደውን ስጦታ ለእግዚአብሔር አመጡ።
ኦሪት ዘጸአት 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 35:4-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች