ኦሪት ዘዳግም 4:32-40

ኦሪት ዘዳግም 4:32-40 አማ05

“እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እናንተ ከመወለዳችሁ በፊት በነበረው ዘመን ያለፈውን ነገር ሁሉ እስቲ መርምሩ፤ ምድርን በሞላ መርምሩ፤ ከዚህ በፊት ይህን የመሰለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ያውቃልን? እንደዚህ ያለውን ነገር የሰማ ከቶ አለ ይሆን? እናንተ በሰማችሁት ዐይነት እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ውስጥ ሆኖ ተናግሮት በሕይወት ለመኖር የቻለ ሕዝብ ከቶ አለን? ወይስ በፈተና፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራ ኀይል፥ በዐይናችሁ እያያችሁት እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ያለ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? አምላክ እርሱ ብቻ እንደ ሆነና ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጥላችሁ ዘንድ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አሳይቶአችኋል፤ እናንተን ለማስተማር ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፤ በምድርም አስፈሪ እሳቱን እንድታዩ ፈቀደላችሁ፤ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ። የቀድሞ አባቶቻችሁን በመውደዱ እናንተን ልጆቻቸውን ስለ መረጣችሁ በታላቅ ኀይሉ እርሱ ራሱ ከግብጽ አወጣችሁ። ይህንንም ማድረጉ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ከእናንተ የሚበልጡትንና ኀያላን የሆኑትን ሕዝቦች አስወጥቶ ምድራቸውን ለእናንተ ርስት ለማድረግ ነው። ስለዚህም በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱ ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤ በልባችሁም ያዙት። እግዚአብሔር አምላካችሁ ለዘለዓለም እንድትኖሩባት በሚያወርሳችሁ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖሩ ዘንድ ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም እንዲሆንላቸው እኔ ዛሬ የማዛችሁን ሕጉንና ትእዛዞቹን ጠብቁ።”