የሐዋርያት ሥራ 8:4-25
የሐዋርያት ሥራ 8:4-25 አማ05
የተበተኑትም አማኞች በሄዱበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ነበር። ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ሄዶ ሰዎቹን ስለ መሲሕ አስተማራቸው። ሰዎቹም የፊልጶስን ቃል በሰሙና የሚያደርጋቸውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በአንድ ሐሳብ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ይድኑ ነበር። ስለዚህ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በከተማይቱ ውስጥ አስማት እያደረገ የሰማርያን ሕዝብ ሲያስደንቅ ቈይቶአል፤ “እኔ ትልቅ ሰው ነኝ!” እያለም ይናገር ነበር። ሰዎች ሁሉ ትንሹም ትልቁም “ይህ ሰው ታላቅ ተብሎ የሚጠራው የእግዚአብሔር ኀይል ነው!” እያሉ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። በጥንቃቄ ያዳምጡት የነበረውም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ያስደንቃቸው ስለ ነበረ ነው። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተናገረውን መልካም ዜና በሰሙ ጊዜ ወንዶችም ሴቶችም አምነው ተጠመቁ። ስምዖን እንኳን ሳይቀር አምኖ ተጠመቀና ከፊልጶስ ጋር ተባባሪ ሆነ፤ የሚደረጉትንም ድንቅ ነገሮችና ታላላቅ ተአምራት በማየቱ ይገረም ነበር። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሰማርያ ላኩአቸው። ስለዚህ የሰማርያ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሄደው ጸለዩላቸው። የሰማርያ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ መንፈስ ቅዱስ ገና በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ፥ እጆቻቸውን በጫኑባቸው ጊዜ ሰዎቹ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ሐዋርያት እጆቻቸውን ሲጭኑባቸው መንፈስ ቅዱስ ለሰዎቹ መሰጠቱን ስምዖን ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥ “እኔም እጄን የምጭንበት ሰው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት በማሰብህ ገንዘብህ ካንተ ጋር ይጥፋ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ አንተ ከዚህ ነገር ክፍል ወይም ዕጣ የለህም። እንግዲህ ከዚህ ከክፋትህ ተጸጽተህ ንስሓ ግባ፤ ምናልባት የልብህን ክፉ አሳብ ይቅር ይልልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን። አንተ በመራራ ቅናት እንደ ተሞላህና የኃጢአት እስረኛ እንደ ሆንክ አያለሁ።” ስምዖንም “አሁን ከተናገራችሁት አንዳች እንኳን እንዳይደርስብኝ እናንተው ራሳችሁ ወደ ጌታ ጸልዩልኝ” አላቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ከመሰከሩና የጌታንም ቃል ከተናገሩ በኋላ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እያበሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

