የሐዋርያት ሥራ 4:13-22

የሐዋርያት ሥራ 4:13-22 አማ05

ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት መናገራቸውን የሸንጎ አባሎች ባዩ ጊዜ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ያውቁ ስለ ነበረ ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩም ዐወቁ፤ የዳነውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ በማየታቸው በእነርሱ ላይ የሚሉትን አጡ። ስለዚህ ከሸንጎው ወዲያ ገለል አደረጉአቸውና በቈይታ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። “እንግዲህ በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን እናድርግ? ይህ ታላቅ ተአምር በእነርሱ እጅ መደረጉ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ታውቆአል፤ ስለዚህ ልንክደው አንችልም። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እየተስፋፋ እንዳይሄድ ከእንግዲህ ወዲህ የኢየሱስን ስም በመጥራት ለማንም እንዳይናገሩ፥ እናስጠንቅቃቸው።” ከዚህ በኋላ ጠሩአቸውና የኢየሱስን ስም በመጥራት ከቶ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ በጥብቅ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ተገቢ ነውን? እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር አንቈጠብም።” የሕዝብ አለቆችና የሸንጎው አባሎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን የሚያስቀጣ ምንም ምክንያት ባለማግኘታቸው፥ ሕዝቡንም ስለ ፈሩ እንደገና አስጠንቅቀው ለቀቁአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግን ስለ ነበር ነው። በዚህ ተአምር የተፈወሰው ያ ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበር።