በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ። እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው። በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ። ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ። እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ። ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤ ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። “ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል። ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው።
የሐዋርያት ሥራ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 13:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች