የሐዋርያት ሥራ 1:12-26

የሐዋርያት ሥራ 1:12-26 አማ05

ከዚህ በኋላ ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም የሚርቀው የሰንበት መንገድ (አንድ ኪሎ ሜትር) ያኽል ነው። ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ወደሚኖሩበት ሰገነት ላይ ወጡ፤ እነርሱም “ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ በርተሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ” ናቸው። እነዚህ ሁሉ ዘወትር ለጸሎት በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር አንዳንድ ሴቶችና የኢየሱስ እናት ማርያም፥ እንዲሁም የኢየሱስ ወንድሞች ነበሩ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መቶ ኻያ በሚያኽሉ አማኞች መካከል ቆመና እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፥ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም ነበረበት። ይሁዳ ከእኛ አንዱ ሆኖ የዚህ አገልግሎታችን ተካፋይ ነበር። ነገር ግን ይህ ሰው በክፉ ሥራው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ተዘረገፈ፤ ይህም ነገር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህ ያ መሬት በቋንቋቸው ‘አኬልዳማ’ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም ‘የደም መሬት’ ማለት ነው። “ይህም የሆነበት ምክንያት በመዝሙር መጽሐፍ፥ ‘መኖሪያው ባዶ ይሁን፤ ማንም አይኑርበት፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰድበት’ የሚል ተጽፎ ስለ ነበር ነው። “ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በተመላለሰበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር አብረውን ከነበሩት፥ እንዲሁም ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ አብረውን ከነበሩት ከነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።” ከዚህ በኋላ ሁለት ሰዎች አቀረቡ፤ እነርሱም በርሳባስ ወይም ኢዮስጦስ የሚባለው ዮሴፍና ማትያስ ነበሩ። እንዲህ ሲሉም ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ጌታ ሆይ፥ ከነዚህ ከሁለቱ ማንን እንደ መረጥክ አሳየን፤ የምንጸልየውም ይሁዳ ወደ ራሱ ስፍራ ሲሄድ የተወውን አገልግሎትና ሐዋርያነት በመቀበል የሚተካውን እንድትገልጥልን ነው።” ዕጣም በጣሉ ጊዜ ዕጣው ለማትያስ ወጣ፤ ስለዚህ እርሱ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።