ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21:1-14

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21:1-14 አማ05

በዳዊት ዘመነ መንግሥት ሦስት ዓመት ሙሉ ጽኑ ራብ ነበር፤ ዳዊትም ስለዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር “ሳኦልና ቤተሰቡ ግድያ በመፈጸም በደል ሠርተዋል፤ ሳኦልም የገባዖንን ሰዎች ፈጅቶአል” ሲል መለሰለት። እንደሚታወቀው ሁሉ የገባዖን ሰዎች እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እነርሱ እስራኤላውያን ሊጠብቁአቸው ቃል ስለ ገቡላቸው ከአሞራውያን ተከፍለው ብቻቸውን የሚኖሩ ነበሩ፤ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ በነበረው ቀኖች ሊያጠፋቸው ዐቅዶ ነበር። ስለዚህም ዳዊት የገባዖንን ሰዎች በአንድነት ጠርቶ “የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትመርቁ ዘንድ ቀድሞ በተፈጸመባችሁ ግፍ ፈንታ ካሣ የሚሆን አንድ ነገር ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ፤ ታዲያ፥ ምን ላድርግላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ከሳኦልና ከቤተሰቡ ጋር ያለን ጥል በብርና በወርቅ የሚገታ አይደለም፤ ከዚህም በቀር እኛ ከእስራኤል ወገን ማንንም መግደል አንፈልግም” ሲሉ መለሱለት። ዳዊትም “ታዲያ ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሳኦል በሙሉ ሊያጠፋንና ከእኛ መካከል ማንም ሰው በእስራኤል ምድር በየትኛውም ስፍራ በሕይወት እንዳይኖር ፈልጎ ነበር፤ ስለዚህ ከሳኦል ዘሮች ሰባት ወንዶችን ለእኛ አሳልፈህ ስጠን፤ እኛም እነርሱን እግዚአብሔር መርጦ ባነገሠው በንጉሥ ሳኦል ከተማ በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንሰቅላቸዋለን” ሲሉ መለሱ። ንጉሥ ዳዊትም “እነርሱን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። ነገር ግን ዳዊትና ዮናታን እርስ በርሳቸው በገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ምክንያት ዳዊት የሳኦልን የልጅ ልጅ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን አሳልፎ አልሰጣቸውም። ይሁን እንጂ ዳዊት የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን ወሰደ፤ እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜራብ የመሖላን ተወላጅ ለሆነው ለባርዚላይ ልጅ ለዐድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጨምሮ ወሰደ። ዳዊት እነዚህን ሁሉ ለገባዖን ሰዎች አሳልፎ ሰጠ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፤ ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ እነርሱም የተገደሉት በጸደይ ወራት ማለቂያና በገብስ መከር መጀመሪያ ላይ ነበር። ከዚህ በኋላ የሳኦል ቊባት የነበረችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ሬሳዎቹ ባሉበት ስፍራ አጠገብ በሚገኘው ቋጥኝ ድንጋይ ላይ ማቅ ዘርግታ ከስሩ ተቀመጠች፤ እርስዋም ከመከር ጊዜ መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ እስከሚጥልበት ጊዜ ድረስ እዚያ ቈየች፤ ቀን ቀን ወፎች በሬሳዎቹ ላይ እንዳያርፉ እየተከላከለች፥ ሌሊት ሌሊትም አውሬ እንዳይበላቸው ትጠብቃቸው ነበር። ዳዊት፥ የሳኦል ቁባት የነበረችው ሪጽፋ ያደረገችውን በሰማ ጊዜ፥ በገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ወደ ያቤሽ ሕዝብ ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም አመጣ፤ የያቤሽ ሕዝብ ዐፅሙን ያገኙት ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉበት ቀን ሬሳዎችን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ በመስረቅ ነበር። ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወሰደ፤ እንዲሁም ተሰቅለው የነበሩትን የሰባቱን ሰዎች አስከሬን ሰበሰበ፤ ከዚህ በኋላ የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወስደው በብንያም ጼላዕ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ውስጥ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ቀበሩ፤ ይህ ሁሉ ከተፈጸመም በኋላ ሕዝቡ ስለ አገራቸው ያቀረቡትን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።