ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:5-13

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:5-13 አማ05

ንጉሥ ዳዊት ወደ ባሑሪም በደረሰ ጊዜ ከሳኦል ዘመዶች አንዱ የሆነው የጌራ ልጅ ሺምዒ ሊገናኘው ወጥቶ እየተራገመ ወደ እርሱ ቀረበ፤ ዳዊት በሠራዊቱና በክብር ዘበኞቹ መካከል እያለ ሺምዒ በዳዊትና በመኳንንቱ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመረ። ዳዊትንም በመራገም የተናገረው ቃል እንዲህ የሚል ነው፦ “አንተ ነፍሰ ገዳይ! አንተ ወንጀለኛ! ከዚህ ውጣ! አንተ የሳኦልን መንግሥት ወሰድህ ቤተሰቡንም ሁሉ ገደልክ፤ እነሆ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር አንተን በመቅጣት ላይ ነው፤ እግዚአብሔር መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ ነፍሰ ገዳይ! እነሆ የአንተ መጥፊያ ደርሶአል።” በዚህ ጊዜ የጸሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን “ንጉሥ ሆይ! ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን እንዴት ይራገማል? እኔ ሄጄ ራሱን ልቊረጠው!” አለው። ንጉሡም አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህ እናንተን አይመለከታችሁም፤ እግዚአብሔር አዞት ቢረግመኝ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ብሎ ለመጠየቅ መብት የሚኖረው ማን ነው?” አላቸው። ቀጥሎም ዳዊት ለአቢሳና ለመኳንንቱ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የራሴ ልጅ ሊገድለኝ ይፈልጋል፤ ታዲያ በዚህ ብንያማዊ ሰው ስለምን ትደነቃላችሁ? እኔን እንዲረግመኝ እግዚአብሔር ነግሮታል፤ ስለዚህ ተዉት፥ የአሰበውን ያድርግ፤ ምናልባት እግዚአብሔር መከራዬን አይቶ በእርሱ ርግማን ፈንታ በረከትን ይሰጠኝ ይሆናል።” ከዚህ በኋላ ዳዊትና ሠራዊቱ ባመሩበት መንገድ ተጓዙ፤ ሺምዒም በኮረብታው ጥግ እነርሱን ተከትሎ እየሄደ በመራገም ድንጋይና ዐፈር በእነርሱ ላይ ይወረውር ነበር።