ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-33

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-33 አማ05

ንጉሡ ዳዊት አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ፤ ስለዚህም በተቆዓ የምትኖረውን አንዲት ብልኅ ሴት አስጠራ፤ እርስዋም በደረሰች ጊዜ “ሐዘንተኛ ለመምሰል ሞክሪ፤ የሐዘን ልብስሽን ልበሺ፤ ቅቤም አትቀቢ፤ ለብዙ ጊዜ በሐዘን ላይ የቈየሽ ሴት ለመምሰል ተዘጋጂ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርበሽ እኔ የምነግርሽን ንገሪው” አላት፤ ከዚህ በኋላ እርስዋ ልትናገረው የሚገባትን ሁሉ ኢዮአብ ነገራት። ሴቲቱም ወደ ንጉሡ ቀርባ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣችና “ንጉሥ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ንጉሡም “ምን ችግር አጋጠመሽ?” አላት፤ እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ሴት ነኝ፤ ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ አንድ ቀን ገላጋይ በሌለበት ስፍራ ሁለቱ ልጆቼ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ አንዱ ሌላውን ገደለው፤ ንጉሥ ሆይ! እነሆ አሁን ዘመዶቼ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው ‘ወንድሙን ስለ ገደለ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን ሰው ስጪን’ እያሉ አስቸገሩኝ። ታዲያ፥ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የቀረኝን አንድ ተስፋ ሊያጠፉብኝና በምድርም ላይ የባሌን ስምና ዘር ሊያሳጡ ነው።” ንጉሡም “ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ አዛለሁ” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! አንተ ስለምታደርገው ነገር ሁሉ እኔና ቤተሰቤ እንወቀስበት አንተና ዙፋንህ ግን ንጹሓን ሁኑ” አለችው። ንጉሡም “ማንም ሰው ማንኛውንም ችግር ቢያመጣብሽ ወደ እኔ አምጪው ዳግመኛ ሊያስቸግርሽም አይችልም” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የልጄን ሞት ለመበቀል ኀላፊነት የተቀበለው ዘመዴ ሌላውን ልጄን በመግደል የባሰ ወንጀል እንዳይፈጽም ታደርገው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ” አለችው። ንጉሥ ዳዊትም “በልጅሽ ላይ ጒዳት መድረስ ይቅርና ከራስ ጠጒሩ እንኳ አንዲቱ መሬት ላይ እንደማትወድቅ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል እገባልሻለሁ” አላት። ሴቲቱም “ንጉሥ ሆይ! እንደገናም እኔ አገልጋይህ አንድ ነገር እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም “እሺ ተናገሪ” አላት። እርስዋም እንዲህ አለችው፤ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ይህን የመሰለ በደል የፈጸምከው ስለምንድን ነው? ልጅህ ከተሰደደበት አገር ተመልሶ እንዲመጣ አልፈቀድክለትም፤ ስለዚህ አሁን በተናገርከው ቃል በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ እኛ ሁላችን መሞታችን የማይቀር ነው፤ እኛ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር ግን በስደት ላይ የሚገኝ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ እንዳይቀር የሚመለስበትን መንገድ ያዘጋጅለታል እንጂ ሕይወቱ በከንቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። አሁንም ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በዚህ ነገር ሰዎች ያስፈራሩኝ መሆኑን ልነግርህ ነው፤ ‘የጠየቅሁትን ሁሉ ያደርግልኛል’ በሚል ተስፋም በፊትህ ቀርቤአለሁ፤ የምነግርህን አድምጠህ ልጄንና እኔን በማጥፋት እግዚአብሔር የራሱ ካደረገው ምድር ሊያስወግደን ከሚፈልገው ሰው ታድነኛለህ ብዬ አስቤ ነው። እንዲሁም ንጉሥ ሆይ! ንጉሥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነና መልካሙን ከክፉው ለይቶ ስለሚያውቅ የተስፋ ቃልህ በሰላም እንድኖር ይረዳኛል ብዬ አስቤ ነው እንግዲህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን!” ንጉሡም “አንድ ጥያቄ እጠይቅሻለሁ፤ አንቺም እውነቱን በሙሉ ንገሪኝ” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የፈለግኸውን ጠይቀኝ” አለችው። እርሱም “ይህን እንድታደርጊ ያዘዘሽ ኢዮአብ ነውን?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም እንዲህ ስትል መልስ ሰጠች፤ “ንጉሥ ሆይ! አንተ ከምትለው ሁሉ ፈጽሞ ሊወጣ የሚችል እንደሌለ በአንተ ስም እምላለሁ፤ በእርግጥም ምን ማድረግና ምን ማለት እንዳለብኝ የመከረኝ የአንተ የጦር አዛዥ የሆነው ኢዮዓብ ነው። እርሱም ይህን ያደረገው ነገሮችን ሁሉ ለማስተካከል በማሰብ ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ጥበበኛ ነህ፤ የሚሆነውንም ነገር ሁሉ ታውቃለህ።” ንጉሡም ዘግየት ብሎ ኢዮአብን “ተስማምቼአለሁና ሄደህ ያንን ወጣት አቤሴሎምን ፈልገህ ወደዚህ አምጣው” አለው። ኢዮአብም በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት በአክብሮት ንጉሡን አመሰገነ፤ “የፈለግኹትን እንዳደርግ በመፍቀድህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አሁን ተረዳሁ” አለ። ተነሥቶም ወደ ገሹር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው፤ ይሁን እንጂ ንጉሡ፥ አቤሴሎም በቤተ መንግሥት ውስጥ እንዳይኖር ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም ንጉሡ “ከቶ እርሱን ማየት አልፈልግም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም በራሱ ቤት ኖረ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም። የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በእስራኤል ምድር ከቶ አልነበረም፤ አቤሴሎም ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ የራሱ ጠጒር እጅግ ብዙ ነበር፤ ስለሚረዝምበትና ስለሚከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የጠጒሩም ክብደት በቤተ መንግሥት ሚዛን ሲለካ ከሁለት ኪሎ በላይ ነበር። አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ነበሩት፤ የሴት ልጁም ስም ትዕማር ሲሆን እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች። አቤሴሎም ንጉሡን ሳያይ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ኖረ፤ ከዚያን በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲጠይቅለት ኢዮአብን አስጠራ፤ ኢዮአብ ግን መምጣት አልፈቀደም፤ አቤሴሎም እንደገና ኢዮአብ እንዲመጣለት መልእክት ላከ፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ፤ ስለዚህም አቤሴሎም አገልጋዮቹን “ተመልከቱ፤ የኢዮአብ እርሻ ከእኔ እርሻ ቀጥሎ ሲሆን የገብስ ሰብል ይገኝበታል፤ ስለዚህም ሂዱና በእሳት አቃጥሉት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሄደው ሰብሉን በእሳት አቃጠሉ። ኢዮአብም ወደ አቤሴሎም ቤት ገሥግሦ ሄደና “አገልጋዮችህ የእርሻዬን ሰብል ያቃጠሉት ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። አቤሴሎምም “አንተ እኔ ስጠራህ ስላልመጣህ ነው፤ ወደ ንጉሡ ሄደህ ‘ከገሹር ወጥቼ ወደዚህ ለምን መጣሁ? እዚያው ቈይቼ ብሆን ኖሮ በተሻለኝ ነበር’ ብለህ ስለ እኔ ሁኔታ ጠይቅልኝ፤ እንዲሁም ከንጉሡ ጋር መገናኘት እችል ዘንድ ሁኔታዎችን አመቻችልኝ፤ እኔ በደለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ሞት ይፍረድብኝ” አለው። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሥ ዳዊት ሄደና አቤሴሎም ያለውን ሁሉ ነገረው፤ ንጉሡም አቤሴሎምን አስጠራ፤ አቤሴሎምም ሄዶ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም ሳመው።