የኤልሳዕ አገልጋይ የሆነው ግያዝ፥ “ጌታዬ ንዕማንን ምንም ነገር ሳያስከፍል አሰናብቶታል፤ ያ ሶርያዊ ሰው ያቀረበለትን ስጦታ መቀበል ይገባው ነበር፤ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፥ በፍጥነት በመሮጥ ተከትየው ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ሲል በልቡ አሰበ። ስለዚህም ግያዝ ንዕማንን ከኋላው ተከተለው፤ ንዕማንም መለስ ብሎ አንድ ሰው እየሮጠ ሲከተለው ባየ ጊዜ፥ ከሠረገላው ወርዶ “ምነው፥ በደኅና መጣህን?” ሲል ጠየቀው። ግያዝም “መምጣትስ በደኅና ነው የመጣሁት፤ ነገር ግን ጌታዬ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖሩ ሁለት የነቢያት ጒባኤ አባላት ድንገት በእንግድነት ስለ መጡበት፥ ሦስት ሺህ ብርና ሁለት መቀየሪያ ልብስ እንድትሰጣቸው እነግርህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” ሲል መለሰለት። ንዕማንም “እንግዲያውስ እባክህ ስድስት ሺህ ብር ልስጥ” ሲል መለሰለት፤ በዚህም አሳቡ በመጽናት ብሩን በሁለት ከረጢት ሞልቶ ከሁለት መለወጫ ልብሶች ጋር በሁለት አገልጋዮች አስይዞ ከግያዝ ቀድመው በፊት በፊቱ እንዲሄዱ አደረገ። ኤልሳዕ ወደሚኖርባትም ኰረብታ በደረሱ ጊዜ፥ ግያዝ ሁለቱን ከረጢት ተቀብሎ ወደ ቤት አስገባ፤ ከዚያም በኋላ የንዕማንን አገልጋዮች አሰናብቶአቸው ሄዱ። ወደ ቤት ተመልሶ ገባ፤ ኤልሳዕም “እስከ አሁን የት ነበርክ?” ሲል ጠየቀው። ግያዝም “ጌታዬ፥ ኧረ እኔ የትም አልሄድኩም” ሲል መለሰ። ኤልሳዕም “ሰውየው ሊያነጋግርህ ከሠረገላው ላይ ሲወርድ እኔ በመንፈስ ከአንተ ጋር አልነበርኩምን? እነሆ አሁን ገንዘብና ልብስ፥ የወይራና የወይን ተክል ቦታ፥ በግና የቀንድ ከብት ወይም አገልጋዮችን ለመቀበል ጊዜው አይደለም! ከዚህም የተነሣ እነሆ፥ የንዕማን የቆዳ በሽታ ወደ አንተ ይተላለፋል፤ አንተና ዘሮችህ ለዘለዓለም ከዚያ በሽታ አትነጹም!” አለው። ግያዝም ወጥቶ ሲሄድ፥ ያ የቆዳ በሽታ ስለ ተጋባበት ገላው እንደ በረዶ ነጭ ሆነ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5:20-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች