ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 22:1-20

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 22:1-20 አማ05

ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የቦጽቃት ከተማ ተወላጅ የሆነው የዐዳያ ልጅ ነበረች፤ ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተልና ለእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ታዛዥ በመሆን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የመሹላም የልጅ ልጅ፥ የአጻልያ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ሳፋንን ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፤ “ሒልቂያ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሂድ፤ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኀላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያኽል ገንዘብ እንደ ሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ ና፤ የመቅደሱን እድሳት ለመቈጣጠር ለተሾሙት ሰዎች ያስረክቡ፤ እነርሱም የተረከቡትን ገንዘብ ቤተ መቅደሱን ለሚጠግኑ፥ ለአናጢዎች፥ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይክፈሉ፤ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሳንቃዎችንና የተጠረቡ ድንጋዮችን ይግዙ፤ የሥራው ኀላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቈጣጠር አያስፈልግም።” ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለሒልቂያ ሰጠ፤ ሒልቂያም “የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ” ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደና “አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል” ሲል አስረዳ፤ ከዚያም ቀጠል በማድረግ፥ “ካህኑ ሒልቂያ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ ይኸው” ብሎ ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወዲያውኑ ለካህኑ ለሒልቂያ፥ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአሒቃም፥ የሚካያ ልጅ ለሆነው ለዐክቦር፥ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፤ “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቈጥቶአል።” ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባልዋ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት። እርስዋም እንዲህ አለቻቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ። እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖቶች ሁሉ እኔን አስቈጥተውኛል፤ ቊጣዬም አይበርድም፤ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፥ ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድ፥ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣው ቅጣት አንተ በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።