አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-21

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-21 አማ05

የዔሊ ልጆች ምንም የማይረቡ ስድ አደጎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያከብሩም ነበር፤ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደዚህ ነበር፦ ሰው ሁሉ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው በመብሰል ላይ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይቀርብ ነበር። እርሱም ሜንጦውን ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦው የሚያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር፤ ይህንንም ድርጊት ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በቀር ጮማው ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መሥዋዕቱን ወደሚሠዋው ሰው መጥቶ “ካህኑ ያንተን የተቀቀለ ሥጋ ሳይሆን ጥሬ ሥጋ ስለሚፈልግ ለእርሱ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉትና ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ትወስዳለህ” ቢለው፥ የካህኑ አገልጋይ “አይሆንም! አሁኑኑ ስጠኝ! እምቢ ብትል ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዐይነት የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ስላቃለሉ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና በልጅነቱ ከበፍታ የተሠራ ሸሚዝ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፤ ይህም ቃል በዕብራይስጡ ካህኑ ለሚለብሰው ልብስ ወይም በደረቱ ላይ ስለሚያደርገው ነገር መጠሪያ ነው። እናቱም በየዓመቱ ባልዋን ተከትላ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናን ከሚስቱ ከሐና ጋር በሚመርቅበት ጊዜ፥ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጋችሁ በሰጣችሁት በዚህ ልጅ ፈንታ ከዚህቹ ሴት ሌሎችን ልጆች ይስጥህ!” ይለው ነበር። ከዚያን በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን አስታወሳትና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ ወጣቱ ሳሙኤልም እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ።