ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ጦርነት ተወግዶ ሰላም ሰፍኖ ነበር፤ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጐብኘት ወረደ፤ አክዓብ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች “በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትን ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዐይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት!” አላቸው፤ ኢዮሣፍጥንም “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ለመዝመት ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው” አለው። “ነገር ግን መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” ሲል መለሰለት። ስለዚህ አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ አደጋ ልጣልባት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት። ኢዮሣፍጥ ግን “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላስ ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይም አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምን ጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም!” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “ይህን ማለት አይገባህም!” አለው። ከዚህ በኋላ አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው። በዚህም ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚጠራው የከናዕና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶችን ይዞ አክዓብን “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’ ” አለው። ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ይሰጥሃል” አሉት። ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደእነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በእግዚአብሔር ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሎአል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር፤ በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ፤ እግዚአብሔርም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’ ” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ እግዚአብሔር ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቈይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ፤ ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቈስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቊስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ፤ ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዐይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሰራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 22:1-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች