አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:3-12

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:3-12 አማ05

ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ። አገልጋዩንም በዚያ ተወው፤ ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጒዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “እግዚአብሔር ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ። ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኀይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም እግዚአብሔር “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም፤ ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ።